ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የአረንጓዴ ልማት መርሀ-ግብር ለሌሎች አገራት ትምህርት የሚሆን ነው- ጃኦ ጎሜዝ ክራቪኝዎ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የአረንጓዴ ልማት መርሀ-ግብር ለሌሎች አገራት ትምህርት የሚሆን ነው- ጃኦ ጎሜዝ ክራቪኝዎ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2016(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የአረንጓዴ ልማት መርሀ-ግብር ለሌሎች አገራት ትምህርት የሚሆን ነው ሲሉ የፖርቱጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃኦ ጎሜዝ ክራቪኝዎ ገለጹ።
የፖርቱጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃኦ ጎሜዝ ክራቪኝዎ ከቀናት በፊት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ሚኒስትሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮ-ፖርቱጋል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው ብለዋል።
የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ፖርቱጋል ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚውና በአራንጓዴ አሻራ ስራ እያከናወነች ያለችው ስራ ዓለማቀፍ ትኩረትን እየሳበና የሚደነቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የልማት መርሃ ግብር እያከናወነች የሚገኘው ሰፊ ተግባርም ለታዳሽ ኃይል ልማት የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ለሌሎች አገራትም ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘው ውጤታማ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ፖርቱጋልና ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የልማት መስኮች በጋራ በመስራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ፖርቱጋል በህዝብ አስተዳደር፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ሌሎች መስኮች የሚሰሩ በርካታ ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ይደረጋል ብለዋል።
የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ፖርቱጋል ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ለአብነትም ከኢትዮጵያ አቻቸው ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር የሁለቱን አገራት የቆየ ዲፖሎማሲያዊ ወዳጅነት አጠናክሮ ማስቀጠል የሚስችል ፍሬያማ ውይይት በማድረግ ከስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በውይይታቸውም በአገራቱ የትብብር ፍኖተ ካርታ መነሻነት ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በሚያጠናክሩ 'ቢዝነስ ፎረሞች' ላይ በጋራ ለመስራት እንደተስማሙም አንስተዋል።
ከቀናት በፊት የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከፖርቱጋል አቻቸው ጃኦ ጎሜዝ ክራቪኝዎ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት የሚያስችል ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል።
የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች የትብብር መስኮች በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ ይታወቃል።