ቀጥታ፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚካሄደው 9ኛው የከተሞች ፎረም በቂ ዝግጅት ተደርጓል- የክልሉ መንግስት

ሶዶ፤ የካቲት 8/2016 (ኢዜአ) ፡- በወላይታ ሶዶ ከተማ ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን 9ኛው የከተሞች ፎረም ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  አስታወቀ። 

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ዛሬ እንደገለጹት 9ኛውን የከተሞች ፎረም ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል። 

ለዚህም የክልሉ መንግስት ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ከወላይታ ዞን እና ከሶዶ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።  

ፎረሙ ከተሞች እርስ በርስ ልምድና ዕውቀት የሚካፈሉበት ከመሆኑ ባለፈ ዕድገትን ለማፋጠን የሚጠቅሙ ተግባራት የሚከወኑበት መሆኑን አስታውሰው፣ በስኬት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። 

በክልሉ ከተሞችን ስማርት ሲቲ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ፣ በፎረሙ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 23 ከተሞች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

መድረኩም ለከተሞቹ ልምድ፣ እውቀትና የመልማት አቅምን የሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

ለፎረሙ ስኬታማነት የክልሉ መንግስት ከዞንና ከከተማ መስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ሰናይት ጠቅሰዋል።   

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ጀገና አይዛ በበኩላቸው ከየካቲት 9 እስከ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው 9ኛው የከተሞች ፎረም በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 


 

ወላይታ ሶዶ ከተማን ከተለያዩ አካባቢዎች ጋር የሚያገናኙ 7 በሮች እንዳሉ ጠቁመው፣ የህዝቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የተረጋጋ እንዲሆን በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ገልጸዋል። 

ለከተሞች ፎረም ስኬታማነት በሰላም እንዲሁም በከተማ ጽዳትና ውበት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ 

ለሁሉም ከተሞች አውደ ርዕይ ማሳያ ቦታ እና የእንግዶች ማረፊያ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው የሶዶ ከተማ ነዋሪዎችም ለእንግዶች አቀባበል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ፎረሙ ለከተማዋ በርካታ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ጠቅሰው፣ "በዋናነት ከሌሎች ከተሞች ጋር ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም የከተማውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል። 

ወላይታ ሶዶ ከተማ አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ ለህዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ በረከት ቶማስ ናቸው።


 

ፎረሙ የኢትዮጵያ ከተሞች በመሆኑ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንግዶችን በመቀበል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

ዘጠነኛው የከተሞች ፎረም “የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ከነገ ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ ለአንድ ሳምንት ይከበራል።

ፎረሙ ነገ በከተማው "ፑንዱኒያ ሜዳ" በተባለ ስፍራ በይፋ የሚከፈት ሲሆን ከፌደራል እስከ ክልልና ወረዳ ያሉ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም