ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ያስመዘገበችው ለውጥ ከኬኒያ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ያስመዘገበችው ለውጥ ከኬኒያ ጋር ያላትን የጋራ ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት እንደሆነ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኪሮሪ ሲንግኦኢ ገለጹ።

ሁለቱ ሀገራት በአቪዬሽን፣ በታዳሽ ሃይል፣ በቴሌኮም እና በወደብ አገልግሎት ዘርፎች ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ትስስርም እየዳበረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ባሳዩት የአመራር ቁርጠኝነት የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት/ፋኦ/ የአግሪ ኮላ ሜዳሊያ መሸለማቸው ይታወሳል።

37ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ለመታደም አዲስ አበባ የሚገኙት የኬኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኪሮሪ ሲንግኦኢ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ያሳየችውን እምርታ የሚደነቀ ነው።

በተለይ በስንዴ ምርት አሁን የደረሰችበት ውጤት በአርኣያነት ጠቅሰው፣ ኬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራትና የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ እንደሆነች ገልጸዋል።

ኬንያ የስንዴ ፍላጎቷን ለማሟላት ከአውሮፓ ሀገራት እንደምታስገባ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን አጠናክራ ከቀጠለች ኬኒያም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንደምትሆን ተናግረዋል።

በዚህም በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በግብርናው ዘርፍ በተለይም የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰጡትን የአመራር ብቃት አድንቀው፣ የአግሪኮላ ሽልማቱን ተገቢነትም ጠቅሰዋል።

የኢትዮ-ኬኒያ ትብብር ከሰላምና ደህንነት ባሻገር ቀጣናዊ ንግድና ኢንቨስትመት ትስስርን በማጎልበት ምጣኔ ሀብታዊ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ በአቪዬሽንና በታዳሽ ኃይል በአንጻሩ ኬኒያ በቴሌኮም እና በወደብ አገልግሎት ባላቸው ዕምቅ አቅም እርስ በርስ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እያጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦችን ሁለንተናዊ ትስስርና ተጠቃሚነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ነው የገለጹት።

በቅርቡ የሚካሄደው የኢትዮ-ኬኒያ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የጋራ ስብሰባ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም