ቀጥታ፡

የቡና ምርታማነት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በምርምር ለመፍታት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2016(ኢዜአ)፡- የቡና ምርታማነት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በምርምር በመፍታት የአምራቾችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ  የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም "የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለኢትዮጵያ ቡና ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ በቡና ምርት እድገት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) አውደ ጥናቱን አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በቡና ምርት የምትታወቅ ቢሆንም በዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አለመገኘቱን ተናግረዋል።

ማህበሩ በዋናነት የቡና አምራቾችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ በቡና ምርታማነት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በምርምር በመታገዝ ለመፍታትና ገቢን ለማሳደግ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሎታው አየለ በበኩላቸው፤ አውደ ጥናቱ ለአራተኛ ጊዜ እንደሚካሔድ አስታውሰው በዕለቱም የቡና ኢንስቲትዩት ለማቋቋም የመሠረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል።

አውደ ጥናቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እና ዲላ ዩኒቨርስቲ በመተባበር  እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

በእለቱ ቡና አልሚዎች፣ አቅራቢዎች፣ ላኪዎች፣ አርሶ አደሮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።

በመሆኑም በዘርፉ ከምርት እስከ ገበያ ድረስ የሚገጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ያለመ የልህቀት ማእከል ማቋቋም እንዳስፈለገ አስረድተዋል።

ሲምፓዚየሙ ለማእከሉ ማስገንቢያ የሚሆን ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ ሲሆን የቡና አልሚዎችን ጨምሮ የተለያዩ በዘርፍ የተሰማሩ አካላት ይሳተፋሉ ተብሏል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም