ለሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ ለመስጠት በመንግሥት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው -ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ ለመስጠት በመንግሥት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው -ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ ፤ የካቲት 7/2016(ኢዜአ)፦ በሁሉም አካባቢዎች ለሕዝቡ ዘርፈ-ብዙ የልማት ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ ለመስጠት በመንግሥት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
"ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በሶማሌ ክልል ደገሀቡር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሁሴን ሀሺ (ዶ/ር)፣ የክልሉና የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች፣ ኡጋዞችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ያከናወናቸው ተግባራት፣ ኃብት የመፍጠር ጉዞ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎችም በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በአካባቢው የሰላምና ፀጥታ ሁኔታው በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዕለት ተለት ሥራችንን ያለምንም ስጋት በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የልማት ጥያቄዎች ስናነሳ ምላሽ አይሰጠንም ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ ግን ምላሽ እያገኘን በመሆኑ ደስተኞች ነን ብለዋል።
በፌደራል እና በክልሉ መንግሥት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ጥሩ ጅምሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በውሃና ኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲሁም የስልክ መስመር ዝርጋታ ላይ በመንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች የሐረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በዲሪ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነቱን እና አብሮነቱን በማጠናከር የዕድገት ጉዞ ተጀምሯል ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ በለውጡ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ለችግሮቹ በሂደት መፍትሔ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ለሕዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በመንግሥት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕዝቡም ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።