በአፍሪካ የትምህርት ስርአት ውስጥ ያለውን የቅኝ ግዛት ትርክት በአፍሪካዊ ታሪክ መተካት ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ትምህርት ስርአት ውስጥ ያለውን የቅኝ ግዛት ትርክት በአፍሪካዊ ታሪክና ትርክት መተካት እንደሚገባ የህብረቱ የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነር ተናገሩ።

ከ44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ጎን ለጎን የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ሞሃመድ ቤሊሆሲን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው የአህጉሪቱ የትምህርት ስርአት ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ፣ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ ተግዳሮቶችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አንስተዋል።

የትምህርት ጥራት፣ መሰረተ ልማት፣ የመምህራን ብቃትና ትምህርት ሰብአዊ መብት መሆናቸውን ተከትሎ አሁን ባሉበት ደረጃ ላይ ትኩረት በማድረግ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በትምህርት ስርአቱ ላይ ያለውን የቅኝ ግዛት ትርክት በመስበር የአፍሪካን ታሪክ ከአህጉሪቱ ትርክት ጋር በማስተሳሰር በአፍሪካ ሃብት ለማስተማር የመምህራንን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በትምህርት ጥራት ዙሪያ የከፋ ችግር መኖሩን ያነሱት ኮሚሽነሩ በአስር አመት የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አስር ህጻናት በአማካይ ዘጠኙ በትክክል ማንበብና ጽንሰ ሃሳብ መረዳት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በዚህም በአፍሪካ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ ግማሽ ቢሊዮን ህጻናት ውስጥ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጉት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በመሆኑም በትምህርት ጥራት፣ በመምህራን ብቃት፣ በመማር ማስተማር ስልት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ እንደሚገባ በአጽንኦት ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ለትምህርት የሚይዙት በጀት ዝቅተኛ መሆን ተጨማሪ ችግር መሆኑን በማስገንዘብ አለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

አህጉሪቱ በ2030 ትምህርትን ለሁሉም ለማድረስ የተቀመጠውን አለም አቀፍ ግብ ለማሳካት 90 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ አባል ሀገራት የትምህርት ፖሊሲያቸውን መሰረት በማድረግ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የመምህርነት ሙያ፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሂሳብ ትምህርቶችን ጨምሮ አስር የድርጊት መርሃ ግብሮችን የያዘ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን አስታወቀዋል።

የዘንድሮው የህብረቱ ጉባኤ "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም