ድርጅቱ ለትግራይ ክልል የ16 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ኮንቴይነሮችን ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ ለትግራይ ክልል የ16 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ኮንቴይነሮችን ድጋፍ አደረገ
መቀሌ፤ የካቲት 07/ 2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የሚያገለግሉና የ16 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ኮንቴይነሮችን ለትግራይ ክልል ድጋፍ አደረገ፡፡
የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ድጋፉን በመቀሌ ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስረክበዋል፡፡
በድርጅቱ የደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረተአብ ተክሉ በርክክቡ ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ጊዜያት ድርጅቱ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
አሁን የተደረገው ድጋፍ ወጣቱን ወደ ሥራ በማስገባት የልማት ተሳታፊ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ ቴክኒክና ሙያ እና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ገብረመድህን ሓጎስ ናቸው።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ ድጋፉ እስከ 120 የሚሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በተደረገው ድጋፍ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ወጣት ለታይ ገብረኪዳን እና ወጣት ዳዊት አብርሃ፣ ለተደረገላቸው ድጋፍ በማመስገን ሰርተው ለመለወጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።
ወጣቶቹ አሁን በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ወደ ስራ ለመግባት እንደሚቸገሩ በመግለጽ፣ የፋይናንስ ድጋፍና የብድር አቅርቦት እንዲመቻችላቸውም ጠይቀዋል፡፡