አፍሪካዊያን ከሚፈትኑ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ቀውሶች ለመውጣት ለአፍሪካዊ መፍትሔ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካዊያን ከሚፈትኑ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ቀውሶች ለመውጣት ለአፍሪካዊ መፍትሔ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2016 (ኢዜአ)፦ አፍሪካዊያን ከሚፈትኑ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ቀውሶች ለመውጣት ለአፍሪካዊ መፍትሔ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የአፍሪካ ኅብረት ገለጸ።
ይህ የተገለጸው እየተካሄደ ባለው በኅብረቱ 44ኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን በተሰጠ ማብራሪያ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የጤና፣ ሰብዓዊ ጉዳዮችና ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ አፍሪካዊያን የጤናና ሌሎች ማኅበራዊ ጠንቆችን ለመከላከል አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያሻ ገልጸዋል።
በአፍሪካ በመልከ ብዙ ግጭቶችና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚሹ ገልፀው፣ ኅብረቱ ተፈናቃዮችን ለመታደግ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ያም ሆኖ መድኃኒትና መድኃኒት ነክ የሆኑ ሰብዓዊ ቁሶችን ተደራሽ ለማድረግ አፍሪካዊ መፍትሄ አዋጭ እንደሆነ ገልፀው፣ አፍሪካ ውስጥ መድኃኒት ማምረት ዘላቂ መፍትሔ መሆኑን አንስተዋል።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የነበረው ችግር አፍሪካ በጤናው ዘርፍ ራሷን መቻል እንዳለባት ትልቅ ትምህርት ሰጥቷል ነው ያሉት።
በመሆኑም የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ ወደ ሥራ ማስገባት፣ ክትባቶች አፍሪካ ውስጥ እንዲመረቱ ማስቻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ስደትና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው፣ በአፍሪካ አገራት መካከል የተፈረመውን የሰዎችና ሸቀጦች ነጻ ዝውውር ሥምምነትን በቁርጠኝነት ሊተገብሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ሰብዓዊ ቀውስና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ባሻገር የአፍሪካ ዳያስፖራ አፍሪካን ማገዝ እንዳለበት ገልጸው፣ የምሁራን ኩብለላም ሌላው መቀረፍ ያለበት ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ ጤናን ጨምሮ በማኅበራዊ ቀውሶች ለመፍታት የጋራ አጀንዳ በማድረግ መተባበርና በአንድ ድምፅ መቆም አለብን ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ በበኩላቸው የአፍሪካ አካታችና ዘላቂ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ ልማት ለማረጋገጥ በትግበራ ላይ ለሚገኘው ለአጀንዳ 2063 ስኬት የሰው ኃብት ልማት ወሳኝ በመሆኑ አፍሪካ በቀል ሥነ-ማስተማር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአፍሪካ 50 በመቶ ሰራተኞች በቂ ትምህርትና ክህሎት እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ ለሰብዓዊ ካፒታል ልማት የሚበጁ የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ መርኃ ግብሮች ለአፍሪካ ሁሉን አቀፍ ልማት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ማብዛትና ደረጃቸውን በማሳደግ አካታችና ጥራት ያለው ትምህርት ሥርዓት መተግበር እንደሚገባ አንስተዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የትምህርት ቤት ምገባ አድንቀዋል።
በዚህም አካታች አሰራሮችን በመተግበር ከትምህርት ቤት ገበታ ውጭ የሆኑ ሕጻናትን መመለስ ይገባል ብለዋል።
በአፍሪካዊያን መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመገንባት በኢኖቬሽንና ትራንስፎርሜሽን፣ የሰዎች ነፃ ዝውውርና የዕውቀት ሽግግር ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የፋይናንስ ክምችትና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካን የዓለም ንግድ ድርሻ ማሳደግ፣ ውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳካት እንዲሁም ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክሎጂ ፈጠራዎችን ማስፋፋት ጉዳዮች አገራት በትኩረት እንዲሰሩባቸው አስገንዝበዋል።
ትምህርትና ሥልጠናን ከሥራ ገበያ ጋር ማጣጣም፣ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ የፖሊሲ መፍትሄዎች እንዲተገብሩ ጠይቀዋል።
አፍሪካ ከዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ድርሻዋ 2 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የግብርና ምርታማነት በማሳደግና እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢኮኖሚያዊ አቅምን መገንባት ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።