የኢትዮ-ተርኪዬ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ሃና አርዓያ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ተርኪዬ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ሃና አርዓያ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ተርኪዬ የቆየ ወዳጅነት እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርዓያ ሥላሴ ገለጹ፡፡
የኢትዮ-ተርኪዬ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርዓያ ሥላሴ፤ የኢትዮጵያና ተርኪዬ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተሳካ መልኩ መቀጠሉን ገልፀዋል።
በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፤ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሙ ለተርኪዬ ባለሃብቶች ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ከተርኪዬ 23 የንግድ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሃብቶች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ሌሎችም ዘርፎች ሰፊ ማብራሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ 200 የተርኪዬ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው 2 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸውን የገለጹት ኮሚሽነሯ ከ20 ሺህ ለሚልቁ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድልም ፈጥረዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምባሳደር በረክ ባራን፤ የሁለቱ ሀገራት የቆየና የረዥም ዓመታት ታሪክ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎችም ዘርፎች የትብብር ግንኙነት ማደጉንም ጠቅሰዋል።
የተርኪዬ ዛካርያ የንግድ ማኅበር ሰብሳቢ ሬድዋን ኡልሶን፤ በቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለሃብቶች ጋር በመወያየት የሚሰማሩበትን የንግድ አማራጭ እንደሚለዩ ገልፀዋል፡፡
በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ዘርፎች ተርኪዬ የካበተ ልምዷን ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሰፊና እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የተርኪዬ ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ ምቹና አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡
በፎረሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምባሳደር በረክ ባራን፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወካዮች እና ከተርኪዬ ዛካርያ ከተማ የመጡ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።