በቅንጅት መስራት - ትውልድን ለማፍራት

                                         (በእንዳለ ደበላ ከሃዋሳ)

መልካም ስነምግባር፣ ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም የተሟላ ስብዕና ያለው ትውልድ ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። ሀገር ያሰበችውን፣ ያለመችውንና የነደፈችውን ዕቅድ ለማሳካትም የሚኖረው አስተዋጾም ቀላል አይደለም። ዛሬ ላይ በቴክኖሎጂ አድገውና ስልጣኔን ተጎናጽፈው ዓለምን እየዘወሩ ያሉ ሀገራት ለእዚህ ደረጃ የደረሱት በዕውቀትና በክህሎት የተካነና የተሟላ ስብዕና ያለው ዜጋ ለማፍራት ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ነው።

በኢትዮጵያም ቀደም ባሉት ዓመታት የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ የተማረ ዜጋ የማፍራት ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈን ተቋማትን የመገንባት ሥራ በስፋት ቢከናወንም ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አንጻር ግን ውስንነቶች ጎልተው ታይተዋል።

በዚህም ምክንያት ተማሪዎች በዕውቀት የተሟላ ስብዕና ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ የተሰራው ስራ ከፈተና ውጤት አንጻር ሲመዘን የጎላ ችግር ያለበት ሆኖ ተገኝቷል። አጥንቶና አውቆ ለፈተና ከመቀመጥ ይልቅ በኩረጃ ተማምኖ የሚፈተነው ተማሪ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ አንድ ማሳያ ነው።

ይህን የትምህርት ስብራት ለመጠገንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት የትምህርት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደሥራ ገብቷል። ይህን ሥራ ለማገዝም ክልሎች ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለይተው በመፍታት ወጣቱ ትውልድ በዕውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ስነምግባር ታንጾ የተሟላ ስብዕና እንዲኖረው ለማድረግ የራሳቸውን ሥራ ጀምረዋል።

በቅርቡ የተመሰረተው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም መልካም ስነምግባር የተላበሰ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። ለእዚህም የትምህርት ስብራትን መጠገን አንዱ የትኩረት መስክ በማድረግ ከወላጆች፣ ከመምህራንና ሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ጀምሯል። ከእነዚህ አካላት ባለፈ በክልሉ የሚገኙ የሴቶችና ወጣቶች ሊግና ሌሎች አደረጃጀቶችም ይህን ሥራ በማገዝ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች በቅርቡ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የትምህርት ሥራ ትልቁ አጀንዳ ይሁን እንጂ በክልሉ ሴቶችና ወጣቶች የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙም ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል። በመደረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በትምህርት ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የዕውቀትና የክህሎት ባለቤት የሆነ ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት ይሰራል። አቶ እንዳሻው እንዳሉት “አምና በተሰጠው የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና እንደ ክልል የመጣው ውጤት ዝቅተኛ ነው። ዘንድሮ ይህን ውጤት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ትምህርት ቀዳሚው ነው። ውጤቱን ለመቀየር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የመምህራንና የትምህርት አመራሩን አቅም ማሳደግ በዋናነት ትኩረት የተሰጠው ነው።

ለእዚህም በተያዘው ዓመት ለ10 ሺህ መምህራን በክልሉ በሚገኙ የዋቸሞ፣ ወልቂጤ እና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ስልጠና መሰጠቱን ነው የገለጹት። መምህራን አቅማቸው በጎለበተ መጠን ለተማሪዎቻቸው የተሟላ ትምህርት በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን ከማንም በላይ አስተዋጾ እንደሚኖራቸውም ነው አቶ እንዳሻው ያመለከቱት።

እንደ እሳቸው ገለጻ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማገዝ የዞንና የወረዳ መዋቅሮች የየራሳቸውን ዕቅድ አውጥተው ወደ ሥራ ገብተዋል። የክልሉ መንግስት የመማሪያ መጻህፍትን  እያሰራጨ እንደሚገኝም ነው የገለጹት። ህብረተሰቡም ገንዘብ በማዋጣት ለትምህርት ዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ወጣቱ በመልካም ስነምግባር የታነጸ እንዲሆን ለማድረግ በክልሉ የሚገኙ የንባብና ሌሎች የክህሎት ማዕከላትን በቁሳቁስ በማደራጀት የማጠናከር ስራ እየተሰራም ይገኛል። ይህም በትምህርት ጥራት ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን የሚያጠናክር ነው። የክልሉ ሴቶችና ወጣቶች ሊግ የትምህርት ስብራቱ ሊጠገን የሚችለው ሁሉም ቅንጅታዊ ሥራ መሆኑን አምነው ይህን ተግባር ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን በመድረኩ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ሊጎች ለትምህርት ሥራው ስኬታማነት በክልሉ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ የሴቶችና የወጣቶች ሊግ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠንክረው እንደሚሰሩም ገጸዋል።

ወጣት ሰንበቶ አባባ የክልሉ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ነው። ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የገጠመ የውጤት ማሽቆልቆል እና የተማሪ ስነምግባር ላይ ለውጥ እንዲመጣ ወጣቱ ከመንግስት ጎን ሆኖ እንዲሰራ ሊጉ የሚጠበቅበትን ይወጣል። የሊጉ አባላት በበጎፍቃድ ሥራዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ የትምህርት ሥራ አንዱ እንደሚሆንም ነው ያመለከተው።

ወጣቶቹ በክፍል ደረጃ የሚበልጧቸውን ታናናሽ ወንድምና እህቶቻቸውን በማስጠናትና በእረፍት ቀናት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የጀመሩትን ሥራ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራም ነው የገለጸው።

ሴቶች ከልጆቻቸው ጋር ካላቸው ቀረቤታ አንጻር በመልካም ስነምግባር እንዲታነጹና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል አስተዋጿቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ኤልሳ ሽመልስ ናቸው። እንደእሳቸው ገለጻ፣ ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ የየዕለት የትምህርት ውሏቸውን በመፈተሽ ለጥናት ጊዜ እንዲሰጡና በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ከማንም በላይ የሴቶች ሚና የላቀ ነው። የሊጉ አባላት በየአካባቢያቸው ይህን በማጠናከር ለትምህርት ዘርፍ ወጤታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሊጉ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። ከእዚህ በተጨማሪ የሊጉ አባላትን በማስተባበር በገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከር ነው ያመለከቱት።

መንግስት የትምህርት ጥራትን በማምጣት ስብራቱን ለመጠገን የጀመረው ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ሊጎቹ ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። በትምህርት ጥራት በተለይ ከተማሪዎች ውጤት ጋር በተያያዘ የተስተዋለውን ችግር መፍታት ለአንድ ወገን ወይም ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። በአገርኛ ብሂል "ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሀኒቱ" እንደሚባለው የለውጥ ሥራው የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። ከቤት ከተማሪ ወላጆች ጀምሮ የመምህራን፣ የማህበረሰብ፣ የትምህርት ቤቶች፣ የአመራሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ተሳትፎ ይጠይቃል።

የትምህርት ስብራቱ እንዲጠገን እነዚህን ባለድርሻ አካላት አስተባብሮ ዘርፉን መምራት ደግሞ ሌላው ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ከእዚህ አንጻር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶችና ወጣቶችን ሊግ በማስተባበር በቅንጅት ለመስራት የታየው ጅምር ይበል ያሰኛል። 

ሀገር በተማረ፣ በመልካም ስነምግባር በታነጸና የተሟላ እውቀትና ስብዕና ባለው ወጣት የምትገነባው በአሁኑ ወቅት በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት መለወጥ ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ባለድርሻ አካላት ሚናቸው የጎላ ነው። በመሆኑም ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት ከቤተሰብ ጀምሮ የትምህርቱን ዘርፍ ማገዝ የሁላችንም መሆን አለበት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም