ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ የመላ አፍሪካውያን የድል ምልክት ነው -አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2016(ኢዜአ)፦የአድዋ ድል መታሰቢያ የመላ አፍሪካውያን የድል ምልክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ተናገሩ። 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት እና ሌሎችም ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የአድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።


 

የኃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉብኝቱ ተገኝተዋል።

በጉብኝቱም ወቅቱ ከነበረው ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት የቀደሙት ጀግኖች ያደረጉትን ትግልና የከፈሉትን መስዋዕትነት በሚመለከት በማሳያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። 

ከጉብኝቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት ያደረጉት ተጋድሎ ለፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ማበብ መሠረት የጣለ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

በደቡብ አፍሪካ፣ በጋና፣ ዚምባቡዌ እና ሊቢያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት በወቅቱ የነበሩ ጀግኖች የነፃነት ትግልና አልሸነፍ ባይነት ለአፍሪካ ነፃነት ጉልህ አሻራ ማኖሩን አንስተዋል።

በተለይም ደግሞ የአድዋ ድል ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን ያረጋገጠ የመላ አፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ አስደናቂ ድልና ዘላለማዊ ኩራት መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚሁ መታሰቢያነት በአዲስ አበባ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያም የመላው አፍሪካውያን የድል ምልክት ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የታደሙ ሁሉ በቀጣይነትም የድል መታሰቢያውን እንዲጎበኙ አምባሳደር ታዬ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን 37ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚካሄድ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም