ቀጥታ፡

የኢትዮ-ተርኪዬ የኢንቨስትመንትና ንግድ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ተርኪዬ የኢንቨስትመንትና ንግድ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርዓያ ሥላሴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምባሳደር በረክ ባራን፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካዮች እና ከተርኪዬ ዛካርያ ከተማ የመጡ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።


 

ኮሚሽነር  ሀና አርዓያ ሥላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያና ተርኪዬ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው።

ከ200 በላይ የተርኪዬ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸው ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ሌሎች የተርኪዬ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በኩል የኢቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻልን ጨምሮ በርካታ ምቹ ዕድሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ብቁ የሰው ሃይል፣ መንግስት ለንግድና ኢንቨስትመንት የሰጠው ትኩረት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎቸ ኢትዮጵያ ካላት ምቹ ሁኔታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምባሳደር በረክ ባራን በበኩላቸው፣ ሁለቱ ሀገራት የቆየና የረጅም ዓመታታ ታሪክ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን አውስተዋል።

የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በንግድ ልውውጥና በሌሎችም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ዘርፎች ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም