ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነትና በሰላም ዙሪያ ያላትን የመሪነት ሚና አጠናክራ መቀጠል አለባት-ምሁራን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነትና በሰላም ዙሪያ ያላትን የመሪነት ሚና 21ኛውን ክፍለ ዘመን በሚመጥን መልኩ አጠናክራ መቀጠል  እንዳለባት ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲሆኑ ተምሳሌታዊ የትግል መቀጣጠል እንዲካሄድ የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንዲቀጣጠል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ፋና ወጊ ሚና ተወጥታለች።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር ደመላሽ መንግስቱ (ዶ/ር)፤ አፍሪካውያን አንድነታቸውን በማጥበቅ የጋራ ተቋማትን ፈጥረው የጋራ አጀንዳዎች ላይ እንዲተጉ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና ሌሎችም የረዥም ዘመን አበርክቶ አድርገዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ጥረት ዘመናትን ተሻግሮ ከለውጡ በኋላም አፍሪካውያን የጋራ ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት የላቀ ሚናዋን በመወጣት ላይ ትገኛለች ብለዋል።


 

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ መሐመድ፤ ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲል፣ የአፍሪካውያን የአሸናፊነት ምሳሌ በመሆን የምትጠቀስ ሀገር መሆኗን ያነሳሉ።

በቀደምት ኢትዮጵያውያን የነበረው አህጉራዊ የመሪነት ሚና የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ትውልድም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቴሶ በበኩላቸው፤ ሌላው ዓለም ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ የድህነት፣ የግጭትና የኋላቀርነት መጥፎ ገፅታ ሰጥቶ መቆየቱን አስታውሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካውያን ችግሮችን በራስ የመፍታት አቅም እንዳላቸው የጋራ አቋም በመያዝ የእሳቤ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልፀዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ለአህጉሪቱ የሚሰጡ የተዛቡ ትርክቶችን በመቀልበስና አፍሪካውያን ይችላሉ የሚል አዲስ ዕይታን በማምጣት ረገድ ኢትዮጵያ ምሳሌያዊ ተግባር እየፈጸመች ነው ብለዋል።

ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ እንደሚሉትም፤ የፖለቲካና ኢኮኖሚ እሽቅድምድም በበዛበት ዓለም ውስጥ የተነጠለ አካሄድ የማያዋጣ በመሆኑ አህጉራዊ አንድነት መፍጠር ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።

ሌላው ዓለም በመጥፎ የሚስለውን አህጉራዊ ገፅታ በመቀየር ረገድ ያለውን እምቅ አቅም በጋራ ጥረት ለምንመኛት አፍሪካ ለውጥ ማዋል ይገባል ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ መሐመድ፤ በዚህ ውስብስብ ዘመንና የውድድር ዓለም ውስጥ አፍሪካን ወደ ብልፅግና እና ጠንካራ አህጉራዊ አንድነት ለማምጣት ቀዳሚው ስትራቴጂ ቀጣናዊ ውህደት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የመሪነት ሚናዋን ታሳቢ ያደረገ አዲስ አፍሪካዊ ንቅናቄ መፍጠርና ተግባራዊ እርምጃዎቿን ማጠናከር እንደሚገባት አመላክተዋል።


 

የኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማምጣትና ሰላምን ለማፅናት ግንባር ቀደም መሆኗ አህጉራዊ ኃላፊነቷን በብቃት እንደምትወጣው ያሳያል ያሉት ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ኮሌጅ መምህርት ሕሊና አሸናፊ ናቸው።

የቀጣናው  ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በባህልና በፖለቲካ ጉዳዮች ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ለተሻለች አፍሪካ መገንባት እንዲተጉ ማስተባበር አለባት ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም