ቀጥታ፡

በሀረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው-አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016 (ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ የተመራ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት የስራ ኃላፊዎች ቡድን በሀረሪ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶችና የጁገል አለም አቀፍ ቅርስ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንክብካቤና ልማት ስራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ እንዳሉት ሀረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እና ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ።

በሀረሪ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመው በተለይም በጁገል የውስጥ ለውጥ መንገድ ስራ በአካባቢው ያለውን ተፈጥሮአዊ ስነምህዳር በመጠቀም ታሪክ፣ ባህልና እሴትን በጠበቀ መልኩ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ በተገኘ ገቢ እየተገነባ የሚገኘው የሀረር ኢኮ ፓርክ ፕሮጀክትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

የሀረር ኢኮ ፓርክ ግንባታ በዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን ፕሬጀክቱ ሲጠናቀቅ ከጅብ ማብላት ትርኢት ባሻገር የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ የሀረሪ ባህል ሙዝየምን፣ የአርተር ራንቦ እና አብደላ ሸሪፍ የግል ሙዚየምን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ  በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ ነገ በሀረሪ ክልል ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም