ቀጥታ፡

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ረቂቅ ፖሊሲ በፍጥነት እንዲጸድቅ አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ረቂቅ ፖሊሲ እንዲፀድቅ የሚያስችሉትን ተግባራት እንዲያፋጥን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት እቅድ  አፈጻጸምን በማዳመጥ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ሀይሌ ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪሱን አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ተሻለ ለውጥ ለማምጣት ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ነጻ፣ ገለልተኛ እና አካታች ሲቪል ሰርቪስ ለመፍጠር፣ የመንግስት አስተዳደርና አደረጃጀት ስርዓትን ለማጠናከር እና የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ለውሳኔ ሰጪነት አቅም ሊፈጥር  በሚችል መልኩ  የሲቪል ሰርቪሱን የሰው ኃይል መረጃ በቴክኖሎጂ እንዲደራጅ መደረጉን አንስተዋል።

የመንግስት አመራሮችንና ሠራተኞችን አቅም ሊያጎለብቱ የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት ሲሰሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ዘርፉ ላይ ካሉ በርካታ ችግሮች አኳያ የተሰሩ ስራዎች አጥጋቢ አለመሆናቸውን በመግለጽ በቀጣይ ሰፊ የቤት ስራ ይጠብቀናል ብለዋል።

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ረቂቅ ፖሊሲ በማዘጋጀት ሰነዱ እንዲጸድቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ተናግረዋል።

ስለ ረቂቅ ፖሊሲውም ከፌደራል እሰከ ወረዳ ለሚገኙ የመንግስት አመራሮች ማብራሪያ በመስጠት ምክክር እንደተደረገበት ጠቅሰው፥ የመንግስት ሰራተኛው በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ፖሊሲው በፍጥነት እንዲጸድቅና ተግባራዊ እንዲሆን የሕግ ማእቀፍ፣ የትግበራ ስትራቴጂ፣ መመሪያዎችና ሌሎች ሰነዶች መዘጋጀታቸውን አክለዋል።

የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፥ ሲቪል ሰርቪሱን ለማዘመን፣ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እና የመንግስት ሰራተኞች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ኮሚሽኑ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው  ብለዋል።

ኮሚሽኑ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ  ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት  በፍጥነት እንዲጸድቅ  አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ  ዜጎች ስለ ፖሊሲው በቂ ግንዛቤ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አክለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ሲቪል ሰርቪሱን ለማዘመን ትልቅ ድርሻ የሚኖረው ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም