ኢትዮጵያ አፍሪካውያን የራሳቸው የአንድነትና የህብረት ተቋም እንዲኖራቸው ትልቁን ሚና ተጫውታለች-አምባሳደር ፍስሐ ሻወል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አፍሪካውያን የራሳቸው የአንድነትና የህብረት ተቋም እንዲኖራቸው ትልቁን ሚና ተጫውታለች-አምባሳደር ፍስሐ ሻወል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም ድርጅቶች በሚቋቋሙበት ወቅት አፍሪካውያን የራሳቸው የአንድነትና የህብረት ተቋም እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና መጫወቷን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻወል ገለጹ።
አምባሳደር ፍስሐ ሻወል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እንዲሁ በዓለም ገናና የዲፕሎማሲ አበርክቶ እንዳላት አውስተዋል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓ፣ ኤስያ፣ መካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ታሪክ እንዳላት አስረድተዋል።
ለዚህም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በማቋቋም ላለፉት 116 ዓመታት በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ሰፊ ሚና መጫወቷን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚቋቋሙበት ወቅት አፍሪካውያን የራሳቸው የአንድነትና የህብረት ተቋም እንደሚያስፈልጋቸው በማመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በማቋቋም ፈር ቀዳጅ ሚና መወጣቷን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አፍሪካውያን ነጻ እንዲወጡና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እንዲቀጣጠል በማድረግ ፋና ወጊ መሆኗን አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ ወቅት በመገኘት ቻርተሩ ሲረቅም ከፍተኛ ሚና ነበራት ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ከዚያም ባለፈ ወደ አህጉርና ወደ ዓለም እየሰፋ የሚሄድ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ይህንን መርህ መሰረት በማድረግ የአፍሪካን አንድነትን የሚያጠናክሩ የንግድ፣ መሰረተ ልማት፣ ህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ስራዎች እያከነወነች ነው ብለዋል አምባሳደር ፍስሐ።
ኢትዮጵያ በአህጉሩ በሰላም፣ በምጣኔ ሃብት፣ በእድገትና በብልጽግና የሚኖራትን የጋራ ተጠቃሚነት ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረትም መርህን መሰረት በማድረግ የጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር የበኩሏን ትወጣለች ነው ያሉት።