የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የኢዜአ እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የኢዜአ እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት የማገዝ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ ገለጹ።
ኢዜአ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በምስልና ድምፅ ቀረፃ፣ በአርትኦትና በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
ኢዜአ በማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ የአገራዊ መግባባትና የገጽታ ግንባታ ስራ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሚያከናውናቸው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተግባራት የዶክመንተሪ/ዘጋቢ ፊልም/ ስፖት፣ የጥናትና ምርምር ሥልጠናዎችንም እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ በሥልጠናው ላይ እንደተናገሩት፤ ኢዜአ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በመረጃ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ተቋማትን አቅም መገንባት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
የመረጃ ልውውጡና ተደራሽነቱን ለማሳለጥ ኢዜአ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ እየገነባ ያለውን አቅም ለማስቀጠል በጋራ የሚሰሩ ተቋማትን ይፈልጋል ብለዋል።
ተቋማት ተያይዘው ሊያድጉ የሚችሉት ለአጋር ተቋማት ያለውን ልምድ ሲያካፍሉና የአገሪቱ የመረጃ ልውውጥና ተደራሽነትን ለማሳለጥ የሚያበርክተውን አስተዋጽዖ ሲያጠናክሩ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢዜአ የሚያካፍለው የረዥም ጊዜ የካበተ ልምድና ክህሎት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተልዕኮና ስኬት አስተዋጽዖ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን በበኩላቸው በሥልጠናው አመራሮቹና ባለሙያዎቹ ኢዜአ ካካበታቸው ልምዶች እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ሰልጣኞቹ የምስልና ድምፅ ቀረፃ፣ የማቀናበርና የኤዲቲንግ ሥልጠናዎችን ለአምስት ቀናት እንደሚከታተሉ በኢዜአ የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንድይራድ አስረድተዋል።
ኢዜአ ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በተለይ የተግባቦት ጽንሰ-ሃሳብ፣ መረጃን ማደራጀትና ማሰራጨት፣ መልዕክት ቀረፃ፣ የፊቸር አጻጻፍ እንዲሁም የተግባቦት ስትራቴጂዎች ላይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ሲሆን፤ በተቋሙ የሚሰጡ ሥልጠናዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።