የሉሲ ቅሪተ-አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ በሚዘጋጁ ኹነቶች ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ኃብቶች የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ ቅሪተ-አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ በሚዘጋጁ ኹነቶች ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ኃብቶች የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦የሉሲ ቅሪተ-አካል የተገኘበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ በሚዘጋጁ ኹነቶች ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ኃብቶች ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሉሲን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ ለአንድ ዓመት የሚቆየው ጉብኝትና መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ይታወቃል።
ይህንንም አስመልክቶ በቅርቡም ከተለያዩ አገራት የመጡ ጎብኚዎችና ተመራማሪዎች ብሔራዊ ሙዚየምን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘት መጀመራቸው ይታወሳል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የሉሲ ቅሪተ-አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመትን አስመልክቶ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጎብኚዎች ወደ አገር መምጣት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በሚካሄዱ መርሃ-ግብሮች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ለማስተዋወቅ እንደ ዕድል የሚጠቀሙበት መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ሉሲን አስመልክቶ ከተሰናዳው ዝግጅት ባሻገር ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ኃብቶች የማስተዋወቅ ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በስፋት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።
መርሃ-ግብሩን በተመለከተ ከአሪዞና ከመጡት አስተባባሪዎች፣ ከአፋር ክልልና ከቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የሉሲን 50ኛ ዓመትን አስመልክቶ በሚዘጋጁ ኹነቶች በአገሪቱ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶችን ለዓለም ማስተዋወቅ በሚያስችሉ የተለያዩ መርኃ-ግብሮች መዘጋጀታቸውንም ነው ያነሱት።
ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ-አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ ሉሲን ያገኟት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰንን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ 28 ጎብኚዎች ብሔራዊ ሙዚየምን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
በአሜሪካ የሚገኘው የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር መገኛ የምርምር ተቋም በዘርፉ የተለያዩ ጥናትና ምርምርን በማካሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ተቋም መሆኑም ይታወቃል።
በአሜሪካ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሂዩማን ኦሪጅን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ለአንድ ዓመት የሚቆይ መርሃ-ግብር ተዘጋጅቷል።
ሉሲ ወይንም ድንቅነሽ ቅሪተ-አካል የተገኘችው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በኅዳር 24 ቀን 1974 መሆኑን ጠቅሰው፤ የ50ኛ ዓመት አከባበር የተጀመረው ከ20 በላይ የሚሆኑ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ነው ብለዋል።
በጉብኝታቸው ብሔራዊ ሙዚየምን፣ የሉሲ መገኛ ቦታ አፋር፣ ኦሞና አርባምንጭ ማቅናታቸውንና ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልፀዋል።
የ50ኛ ዓመቷን ለማክበር የተለያዩ መርሃ-ግብሮች መሰናዳታቸውን ገልጸው፤ ሐምሌ ላይ ከ200 በላይ ሳይንቲስቶች የሚሳተፉበት የሦስት ቀን ጉባዔ እንዲሁም የፎቶ ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ይካሄዳል ብለዋል።
በዚህም ሌሎች የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስተዋወቅና የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳደግ ይሰራል ነው ያሉት።
የሉሲ ቅሪተ-አካል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ከአሁን ጀምሮ እስከ ቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ሲምፖዚየሞች፣ የፎቶግራፍ አውደ-ርዕይን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚዘከር መሆኑን አመልክተዋል።
ሉሲ ወይም ድንቅነሽ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት ያላት የሰው ልጅ ቅሪተ-አካል ስትሆን፤ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ኅዳር 24 ቀን 1974 አፋር ውስጥ በሚገኝ "ሀዳር" የተባለ ቦታ መገኘቷ መረጃዎች ያመለክታሉ።