የአፍሪካ ሀገራት አካታችና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- አልበርት ሙቻንጋ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት አካታችና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- አልበርት ሙቻንጋ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ሀገራት አካታችና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አመለከተ።
44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ በአፍሪካ አካታችና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ ሀገራት በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።
በአፍሪካ በሥራ ገበታ ላይ ካለው የሰው ኃይል መካከል 15 ነጥብ 8 በመቶው በበቂ ደረጃ ተፈላጊውን ክህሎት ይዘው እየሰሩ አለመሆኑን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ጠቅሰዋል።
ሥራ ፈላጊው እና በአፍሪካ ያለው የሥራ ገበያ አለመጣጣም አህጉሩን እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው ሀገራት መሰል ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ፖሊሲና አሰራር ሊዘረጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ 2 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ይህም የአፍሪካ ሀገራት ምርትን በበቂ መጠን እያመረቱ አለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
በመሆኑንም የግብርና ምርትን ማሳደግ፣ የተቀነባበሩና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን በስፋት ማምረትና ለዓለም ገበያ ማቅረብ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አምራች ዘርፉ ለአፍሪካ አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት ዕድገት /ጂ ዲ ፒ / የ11 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው በመስኩ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በአፍሪካ በኢኮኖሚ መስክ አካታችና ዘላቂ እድገት ለማምጣት ከአፍሪካ ኀብረትና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመሆን መፍትሄ ጠቋሚ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ጥናቱ በአፍሪካ የሰው ኃይል ልማት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ መሆኑን አብራርተዋል።
ጥናቱ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ሀምሌ 2024 የሚጠቀናቀቅ ሲሆን የአፍሪካን የዓለም ንግድ ድርሻ ማሳደግና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳካት ከያዛቸው ጥቅል ግቦች መካከል ይገኝበታል ብለዋል።
ኮሚሽነር አልበርት በማብራሪያቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክሎጂ ፈጠራዎችን ማስፋፋት ቁልፍ በመሆናቸው ሀገራት አጽንኦት ሊሰጧቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።