የአፍሪካን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገውን መዋዕለ ንዋይ ማስፋት ይገባል - ክላቨር ጋቴቴ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገውን መዋዕለ ንዋይ ማስፋት ይገባል - ክላቨር ጋቴቴ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገውን መዋዕለ ንዋይ ማስፋት እንደሚያስፈልግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።
በ44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ በአዲስ አበባ የሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ተጀምሯል።
በስብሰባው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ፣ የአገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ፤ በስብሰባው ላይ አህጉራዊ የማኅበረ-ኢኮኖሚ ግቦችን ለማሳካት ትምህርት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
አህጉራዊ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ የአፍሪካን ሁለንተናዊ ልማት ማሳለጥ እንደሚያስቸግርም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ የትምህርት ሥርዓት ላይ ቀሪ ስራ እንደሚጠይቅ ጠቁመው፤ የአህጉሪቷ መሪዎች በ1960ዎቹ በቅኝ ግዛት የትምህርት ሥርዓት ላይ የሚያነሱት ጥያቄ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
በዓለም የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁነቶች የተሻለ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘመናዊ ግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል ሥርዓት፣ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ እና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ለበርካታ የኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስኬት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምህንድስና እና ሒሳብ የትምህርት መስኮች ቀጣይነት ያለውና ክህሎት የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
በአፍሪካ ያለውን አጠቃላይ መደበኛ ትምህርት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ጋር አቀናጅቶ ማስተማር ለፈጠራ ሥራ መሰረት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ ውጤታማ የትምህርት ስርዓትን ተደራሽ በማድረግ ምርታማነትንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማደረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ለብዝሃ ኢንዱስትሪላይዜሽንና ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት መመደብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትልምን እውን ለማድረግም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በፈጠራ የተደገፈ የክህሎት አብዮት ያስፈልገናል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሕብረቱ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።