በወሊሶ ከተማ ለነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወሊሶ ከተማ ለነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ወሊሶ፤የካቲት 06/2016 (ኢዜአ)፡-በወሊሶ ከተማ ለነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን መዲናዋ ወሊሶ ባላት ሀብትና ታሪክ ልክ ልማትና እድገት አላስመዘገበችም።
በተለይም ለነዋሪዎቿ ምቹና የተሟላ መሰረተ ልማቶች በማሟላት ረገድ ገና ብዙ ስራ የሚጠብቃት መሆኑን ኢዜአ ከተማዋን በመቃኘት ለመረዳት ችሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የከተማዋ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበር ትልልቅ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል።
የወሊሶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ነጌሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ ገቢ፣ በክልሉ መንግስት በጀትና በግበረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል ክልሉ በመደበው 371 ሚሊዮን ብር በጀት እየተገነባ ያለውን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ያነሱት አቶ ፍቅሩ፤ ፕሮጀክቱ በሀገር ደረጃም ከሚጠቀሱ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች አንዱና ለቀጣዩ 50 ዓመታት ለነዋሪው የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
ለፕሮጀክቱ ዘጠኝ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው መጠናቀቃቸውንና አጠቃላይ ግንባታው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አክለዋል።
የውስጥ ለውስጥ የኮብል ድንጋይ የመንገድ ግንባታዎችና ድልድዮችም ሌሎች በከተማዋ እየተፋጠኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ነው ያነሱት ምክትል ስራ አስኪያጁ።
ሌላው አራት የግንባታ ምዕራፎች ያሉትና የከተማዋን ደረጃ ከፍ ያደርጋል የተባለለት ሰፋፊ የመንገድ ዳር ፓርኮች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን አንስተዋል።
ሊበን ፓርክ በሚል ስያሜ እየተገነባ ያለው መንገድ ዳር የማስዋብ ስራ ምቹ የማረፊያ ስፍራዎች፣ የህዝብ ቤተ መጻህፍት፣ የውሃ ፋውንቴኖችና ሌሎች ግንባታዎችን በውስጡ መያዙን ተናግረዋል።
የፓርኩ ግንባታ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለተደራጁ ወጣቶች የተሰጠ ሲሆን፤ የፓርኩ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሌሊሳ በቀለ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የህዝብ ቢሆንም ለራሳቸው ለወጣቶቹ የልምድ መቅሰሚያና ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ተናግሯል።
ሰባት ሆነው መደራጀታቸውን የገለጸው ኢንጅነር ሌሊሳ፤ ከትምህርት ቤት ባገኙት እውቀትና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ በፓርኩ በርካታ የመዝናኛ ዓይነቶች እንደሚገነቡ ገልጿል።
በኦሮሚያ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮ ባለቤትነት እየተገነባ ያለው ወሊሶ የተቀናጀ የመናኻሪያ ግንባታም የከተማዋን ደረጃ ከፍ ከሚያደርጉ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
የመናኻሪያው ግንባታ ተቋራጩ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ጫኔ እንደሚሉት፣ ፕሮጀክቱ 265 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለትና ለወሊሶና በመስመሯ ላሉ ከተሞች የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
በ1919 ዓ.ም የተመሰረተችው ወሊሶ ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ በ114 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።