ኢትዮጵያ አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጠየቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጠየቀች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2016(ኢዜአ)፦ አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በኩል ጥሪ አቀረበች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጥያቄ ያቀረቡት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ ከአፍሪካ የ2063 አጀንዳ ጋር የሚጣጣም መሆኑን አንስተዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን አገር በቀል ቋንቋዎች ለማጠናከር የተያዘውን የአፍሪካ ኅብረት ግብ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑንም ነው በማብራሪያቸው ያነሱት።
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር የተፈረመው አማርኛን ጨምሮ በአራት ቋንቋዎች መሆናቸውን ያነሱት አምባሳደር ታዬ አማርኛን የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ ማድረግ የአፍሪካ የቋንቋ ብዝኃነት መቀበልና የጋራ ማንነትን ማጠናከር ነው ብለዋል።
ይህም አህጉሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እገዛ እንደሚያደርግ በመጠቆም።