ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል--ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል--ሚኒስቴሩ
ሶዶ ፤ የካቲት 6/2016 (ኢዜአ) -ባለፉት ስድስት ወራት ወደውጭ ከተላኩ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የዘርፉን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ ገምግሟል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በመድረኩ እንዳሉት፣ ገቢው የተገኘው ወደውጭ ከተላኩ ቅመማ ቅመም፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎች የግብርና ውጤቶች ነው።
የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንዲቻል መስፈርት የወጣላቸው 22 የምርት ዓይነቶችን ናሙና በመውሰድ የምርት ጥራትን የማረጋገጥ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በእዚህም ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ያመረቱና ያቀረቡ አምራችና ነጋዴዎች ላይ ሚኒስቴሩ እርምጃ መውሰዱን ነው አቶ ገብረመስቀል የገለጹት።
ዘመናዊና ተደራሽ የንግድ አሰራርና የሸማቾች ጥበቃ ስርዓት ለማስፈን በተደረገ ጥረትም 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ህገ-ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል እንዲቻል በሁሉም አካባቢዎች ህብረተሰቡን ባሳተፈና ወጥነት ባለው መልኩ ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር እንደሚዘረጋም አመላክተዋል።
እንደ ሀገር እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አቶ ገብረመሰቀል ገልፀዋል፡፡
የግብርና ምርቶች በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች በማቅረብ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ትኩረት የተደረገበት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የቅዳሜና እሁድ ገበያ በከተሞች ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከግብርና ውጤቶች ባሻገር የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል እንዲቀርቡ ማድረጉ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ማገዙንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሸማቾች ህበረት ሥራ ማኅበራት ራሳቸው ገበያን በማረጋጋት የበኩላቸውን እንዲወጡ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ ይሰራል ብለዋል።
ህገ-ወጥ ንግድ የኑሮ ውድነት ከማባባስ ጀምሮ የወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ሁሉም ከመንግስት ጎን ሆኖ ድርጊቱን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ የሁሉም ከልል ንግድና ልማት ቢሮ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎች በወላይታ ዞን አባላአባያ ወረዳ በአንድ ባለሀብት በ550 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን እንደሚጎበኙ ታውቋል።