በሐረሪ ክልል ነገ ህዝባዊ ውይይት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ነገ ህዝባዊ ውይይት ይካሄዳል
ሐረር ፤ የካቲት 6/2016 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በወቅታዊ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት ነገ በሐረር ከተማ ይካሄዳል።
የፌዴራል ከፍተኛ የአመራር አባላት ነገ በሐረሪ ክልል ለሚካሄደው ህዝባዊ ውይይት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ሐረር ከተማ ገብተዋል።
መንግስት ያጋጠሙ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በተለያዩ አካባቢዎች ህዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በተለይም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶች መነሻ የሚሆኑ ነጠላ ትርክቶችን በአሰባሳቢ የጋራ ትርክቶች ለመተካትና ስብራቶችን ለመጠገን የህብረተሰቡ ሚና የጎላ መሆኑን በማመን ሕዝባዊ ውይይቶችን እያካሄደ ነው።
ባለፉት ሳምንታት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ባሉ ዋና ዋና ከተሞች የተካሄደው ህዝባዊ ውይይትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
በሐረሪ ክልልም በወቅታዊ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት ነገ ይካሄዳል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ የአመራር አባላትም ነገ በሐረሪ ክልል የሚካሄደውን ህዝባዊ ውይይት መድረክ ለመምራት ነው ሐረር ከተማ የገቡት።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌን ጨምሮ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድርና ሌሎች አመራሮች ይገኙበታል።
የአመራር አባላቱ ድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ፣ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላምና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ ነገ በሐረሪ ክልል ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ከውይይቱ በተጓዳኝ የአመራር አባላቱ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ስራዎችንና የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ይጎበኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።