ቀጥታ፡

ተልዕኳቸውን በጀግንነት ፈጽመው ለተመለሱ ልዩ የፀረ-ሽብር አመራርና አባላት ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5/2016(ኢዜአ):- ተልዕኳቸውን በጀግንነት ፈጽመው ለተመለሱ ልዩ የፀረ-ሽብር አመራርና አባላት በኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ ፀረ ሽብር መምሪያ አመራርና አባላት በተለያዩ ግዳጆች ላይ ከአራት ዓመታት በላይ ቆይተው ሲመለሱ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታና የማኔጅመንታቸው አባላት በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የልዩ ፀረ-ሽብር አባላቱ የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተልዕኮ ላይ ቆይተው አሁንም ለሌላ ፖሊሳዊ ተልዕኮ እንደተመለሱ ታውቋል፡፡


 

የልዩ ፀረ-ሽብር ኃይሉ ያካበተውን ልምድና ሙያዊ ብቃት ተጠቅሞ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ በፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድና በመቆጣጠር በርካታ ድሎችን ሲጎናፀፍ የቆየ መሆኑን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የልዩ ፀረ-ሽብር ኃይል አመራርና አባላትም በቀጣይ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በጥሩ ፖሊሳዊ ሙያና ስነ-ምግባር ለመፈፀም የተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም