ለሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መተላለፉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ለሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መተላለፉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2016(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ለሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መተላለፉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማእድን ዘርፍ ለተሰማሩ 14 ኤክስካቫተር፣ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ 28 የቱር ኦፐሬተር መኪኖች እና ለኮንስትራክሽን ስራ የሚሆኑ 7 ሎደሮች ለደንበኞቹ በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው፤ በርክክቡ ላይ ባደረጉት ንግግር የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
በቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን እንዲሁም በማዕድን ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያደርገው ድጋፍ በየጊዜው እያደገ መሆኑንም አንስተዋል።
ከአራት አመታት በፊት ይሰጥ የነበረው 4 ነጥብ 3 ቢልዮን ብር እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ በስድስት ወራት 10 ቢሊዮን ብር መሰጠቱን ተናግረዋል።
የሊዝ ፋይናንሲንግ በብድር አመላለሱም በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው የተላለፉት ማሽነሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የተበላሸ ብድር መጠን 36 በመቶ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ወደ 1 ነጥብ 6 በመቶ መውረዱን ተናግረዋል።
ባንኩ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች እንዲሁም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች እንዲረዱት በማድረግ የተገኘ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።
ተጠቃሚዎችም የተረከቧቸው ማሽነሪዎች እያከናወኑ ያሉትን ስራዎች በተጠናከረ አቅም ለመስራት የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላለፉት 115 ዓመታት የሀገርን ኢኮኖሚያዊ እድገት በመደገፍ ላይ የሚገኝ የፖሊሲ ባንክ መሆኑ ይታወቃል።