ቀጥታ፡

ለሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ምዕራፍ ትግበራ የአጋርና ለጋሽ አካላት ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2016 (ኢዜአ)፦ የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ምዕራፍ ትግበራ እንዲሳካ የአጋርና ለጋሽ አካላት የገንዘብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።

የሰቆጣ ቃልኪዳን በኢትዮጵያ የሕፃናት መቀንጨርን ሙሉ ለሙሉ የማስቀረት አላማ የሰነቀ ፕሮግራም ነው።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ለሚተገበረው የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ምዕራፍ 146 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ዛሬ ይፋ በተደረገው የሀብት ማሰባሰቢያ እቅድ መድረክ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።


 

ዶክተር ደረጀ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ የሰቆጣ ቃልኪዳን በምግብ እና በስርዓተ ምግብ እጥረት የሚከሰትን የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይና አማራ ክልሎች አዋሳኝ 40 ወረዳዎችን በማቀፍ የተጀመረው ፕሮግራሙ በፈረንጆቹ 2021 ያቀፋቸውን ወረዳዎች ወደ 240 በማሳደግ ለብዙ ሀገራት ምሳሌ የሆነ ተጽዕኖ መፍጠሩንም ጠቅሰዋል።

ከአጋዥ አካላት ጋር በመተባበር ማህበራዊ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም በየጊዜው የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ፈታኝ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በመንግስት የተለያዩ ፕሮግራሞች በመተግበር ላይ መሆናቸውን ጠቁመው የአጋር አካላት ጠንካራ ተሳትፎና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራ ባለበዙ ዘርፎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ በስርዓተ ምግብ ላይ ለውጥ ያመጣ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ከመቀንጨርና ከሞት የታደገ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በዚህም ሀገራዊ የመቀንጨር ምጣኔ ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረበት 58 በመቶ አሁን ወደ 39 በመቶ መቀነሱን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ መቀንጨርን ሙሉ ለሙሉ የማስቀረት አላማ የሰነቀው የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ምዕራፍ ትግበራ እንዲሳካ የአጋርና ለጋሽ አካላት የገንዘብ ድጋፍ ተጠናክረሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


 

የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮጀክት ማናጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ፤ እስከ 2021 በነበረው የመጀመሪያው ዙር ትግበራም 59 ሺህ 717 ህፃናትን ከመቀንጨር እንዲሁም 2 ሺህ 900 በላይ ህፃናት ከሞት ታድጓል ብለዋል።

የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ትግበራ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋት በ2025 መጨረሻ በ700 ወረዳዎች ተደራሽ በማድረግ 199 ሺህ 839 ህፃናትን ከመቀንጨር ይታደጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በ10 ዓመታት የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ምዕራፍ ፍኖተ ካርታ የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን ለመተግበር 146 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ነዋይ ይጠይቃል ብለዋል።


 

በዚህም በየዓመቱ የክልሎችን መዋጮ ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግስት በዓመት 6 ቢሊዮን ብር በጀት በተመሳሳይ ከለጋሽ እና አጋር አካላት 6 ቢሊዮን ብር በድምሩ 12 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙ የተለያዩ አጋር አካላት ተወካዮችም ለቀጣይ ምዕራፍ ስኬት ቃል የገቡትን ድጋፍ እንደሚፈጽሙ አረጋግጠዋል።

የሪዛልት ፎር ዴቬሎፕመንት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዮሴፍ አለሙ፣ የዓለም ሕጻናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎንሺማ፣ የዩኤስኤ አይዲ የኢትዮጵያ ተጠሪ ስኮት ሆክላንደር ድርጅቶቻቸው ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋገጠዋል።

የሰቆጣ ቃልኪዳን እ.አ.አ 2015 እስከ 2030 ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን መቀንጨር ዜሮ ለማድረስ ግብ ተይዞለት በትግበራ ላይ የሚገኝ ሀገር አቀፍ ፕሮግራም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም