ለፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች ወቅቱን የዋጀ ስታቲስቲክስ መረጃ ለማቅረብ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ለፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች ወቅቱን የዋጀ ስታቲስቲክስ መረጃ ለማቅረብ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2016(ኢዜአ)፦ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ውሳኔ ሰጪዎችና ለኅብረተሰቡ ወቅቱን የዋጀ የስታትስቲክስ መረጃ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ ከኖርዌይ ስታትስቲክስ ጋር በመተባበር ለተቋሙና ለአጋር ተቋማት ሠራተኞች ለሦስት ቀናት የሚቆይ የስታትስቲክስ መረጃን በተመለከተ የኮሙኒኬሽንና አድቮኬሲ ሥልጠና እየሠጠ ነው።
በስልጠናው የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኖርዌይ ስታቫንገር ዩኒቨርሲቲ የመስኩ ምሁር ፕሮፌሰር ጆ ሮስሌን የስታቲስቲክስ መረጃ ጠቃሚነት ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።
በተለይም መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የመስኩ ባለሙያዎች አውድን የዋጀ የአቀራረብ ሥልት መከተል እንዳለባቸው ተናግረው በመስኩ የተሰማሩ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ማጠናከር አለባቸው ነው ያሉት።
በተለይም የስታትስቲክስ መረጃዎች ተደራሽ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ራሳቸውን በክህሎት ከማብቃት ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን ስለ ስታትስቲክስ መረጃ ጠቃሜታ እውቀት የማስጨበጥ ድርብ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የስታቲስቲክስ ማዕከል የዘርፉ ባለሙያ ሌንድሬ ንጎጋንግ በበኩላቸው በአፍሪካ የስታቲስቲክስ መረጃዎች በአግባቡ ተደራሽ በማድረግ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ብለዋል።
የስታቲስቲክስ መረጃን የሚያቀርቡ አካላት መረጃዎችን በሙያ ቃላትና አገላለጽ ከመቅረባቸው በዘለለ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴን ያላገናዘበ አቀራረብ እንዳላቸው ይስተዋላልም ነው ያሉት።
ይህ አይነቱ አቀራረብ የስታቲስቲክስ መረጃን የሚጠቀሙ አካላትን ፍላጎት ከግንዛቤ ያላስገባ በመሆኑ ተጠቃሚዎች በቀላሉ መረጃውን እንዳያገኙ እንደሚያደርጋቸው ነው የገለጹት።
ችግሩን ለመቅረፍም የዘርፉ ባለሙያዎች ክህሎታቸውን በማዳበር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና የተለያዩ የአቀራረብ ሥልቶችን በመጠቀም የስታትስቲክስ መረጃዎች በቀላሉ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ስታቲስቲክስ መረጃዎች በተደራጀ መልኩ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር)፤ ተቋሙን ጨምሮ በዘርፉ በተሰማሩ አካላት በተለይም በኮሙኒኬሽን ሥራዎች ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ተለይቷል ብለዋል።
ይህንን ከግምት በማስገባት ተቋሙ የሚሰበስባቸውና የሚያሰራጫቸውን የስታትስቲክስ መረጃዎች ወቅታዊ፣ ታአማኒና ግልጽ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ ስራ አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ዛሬ ለተቋሙ ሠራተኞችና አጋር ተቋማት ባለሙያዎች የተጀመረው ሥልጠና የዚሁ ሪፎርም አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም ስትራቴጂ በመንደፍ፣ ከአጋር አካላት ጋር ያሉ ቅንጅታዊና የአሰራር ሥርዓቶችን የመፈተሽና የማስተካከል ሥራዎችን በማከናወን በዘርፉ ጠንካራ የኮሙኒኬሽን ሥራ ለማከናወን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።