ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማስቀደምና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት በልዩ ትኩረት እየሰራሁ ነው-  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማስቀደምና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጹ። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ክብር፣ አንድነት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ ሀገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ የተለየ አቋም እንደሌለው ያምናሉ። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም የተቋቋመበት ዋነኛ አላማ በነዚሁ ጉዳዮች ዙሪያ ለመስራት መሆኑን ጠቁመው በተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቷ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአት እንዲገነባና በፖለቲካ ፉክክሩም በሃሳብ የበላይነት የማሸነፍ ባህል እንዲስፋፋ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አሁን ላይ በተለይም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና በሰላም ጉዳይ ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ሰብሳቢው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም ፓርቲዎች በሀገር ብሄራዊ ጥቅምና በሰላም ጉዳይ የተለየ አቋም ሊኖራቸው አይገባም ብለዋል።

የህዝቡም ፍላጎት ሰላምና ልማትን እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በዚሁ መልኩ መንቀሳቀስ አለብን ነው ያሉት።


የጋራ ምክር ቤቱ አባልና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር፤ ፓርቲያቸው በሰላም ጉዳይ ላይ አበክሮ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም የድርሻችንን ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅብናልም ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም