ቀጥታ፡

37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል- የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2016 (ኢዜአ)፦ 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል እስከአሁን ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የፀጥታ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን ገምግሞ፤ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔም በሰላም እንዲጠናቀቅ በርካታ የፀጥታ ኃይል አሰማርቶ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና ደኅንነት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ገልጿል።

በተከታታይ እየተካሄደ ያለው የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን አዲስ አበባ ከተማ ፍፁም ሰላማዊ ሆና እንድትቀጥል ያስቻለና አሁን ላይም የከተማዋ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መቀጠሉን በግምገማ ያረጋገጠ መሆኑን በመግለጫው አመላክቷል።

ግብረ-ኃይሉ ባካሄደው ግምገማ እስከአሁን ለተገኘው ሰላም እና በተካሄደው ኦፕሬሽን ለተገኘው ውጤት የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር ብሏል መግለጫው።

አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ሕብረት እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ፀጥታዋ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ግብረ-ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ መግለጫው አንስቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ሀገር ሁሉም የፀጥታ መዋቅር የሚመለከተውን የሥራ ድርሻ ወስዶ አካባቢውን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ በኃላፊነትና በተጠያቂነት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ መግለጫው ጨምሮ ገልጿል።

በጉባዔው ላይ የሚታደሙ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ወግና ባህል በመቀበል እና በማስተናገድ በቆይታቸው ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ፤ ካረፉባቸው ሆቴሎች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚሄዱበት ወቅት ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን በባለቤትነት የሚጠበቅበትን የዜግነት ድርሻውን በኃላፊነት እንዲወጣና ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

የካቲት 05 ቀን 2016 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም