የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ትግበራ የሀብት ማሰባሰቢያ ዕቅድ ይፋዊ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ትግበራ የሀብት ማሰባሰቢያ ዕቅድ ይፋዊ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2016 (ኢዜአ)፡- የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ትግበራ የሀብት ማሰባሰቢያ ዕቅድ ይፋዊ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ምዕራፍ ትግበራው በድምሩ 146 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2015 በይፋ መተግበር የጀመረው የሰቆጣ ቃልኪዳን በፈረንጆቹ 2030 ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የመቀንጨር ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ ግብ ይዞ የሚተገበር የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮግራም ነው።
በፈረንዶቹ 2015 በሰቆጣ ከተማ 40 ወረዳዎችን በማቀፍ የተጀመረው ፕሮግራሙ በ2021 ያቀፋቸውን ወረዳዎች ወደ 240 በማሳደግ ለብዙ ሀገራት ምሳሌ የሆነ ውጤታማ አፈፃፀም እንደነበረው ተወስቷል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮጀክት ማናጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ እንዳሉት እስከ 2021 በነበረው የመጀመሪያው ዙር ትግበራ 59ሺህ 717 ህፃናትን ከመቀንጨር እንዲሁም 2ሺህ 900 በላይ ህፃናት ከሞት ታድጓል።
ከ2021 እስከ 2030 በሚተገበረው ሁለተኛ ዙር የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ፕሮግራም የሚተገበርባቸውን ወረዳዎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋት በ2025 መጨረሻ 700 ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፤ 199ሺህ 839 ህፃናትን ከመቀንጨር እንደሚታደግ ተገልጿል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን በተለይም በጤና፣ በትምህርትና በግብርናና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ብሔራዊ የምግብና የስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ትግበራ ላይ ያተኮረ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንዳሉት የሰቆጣ ቃልኪዳን የደጋፊ አካላት ሀብት ማሰባሰብ ለፕሮግራሙ ስኬት ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ በጤናና በማህበራዊ ዘርፎች በመንግሥትና በአጋዥ አካላት ትብብር በርካታ ለውጦች እያስመዘገበች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በትውልድ ግንባታ ላይ ለሚተገበሩ ፕሮግራሞች የአጋር አካላት የተጠናከረ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።
መንግስት የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና ችግርን ለመቅረፍ በርካታ ፕሮግራሞችን በመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።
ለዚህም የሰቆጣ ቃልኪዳን ባለፉት አስርት ዓመታት ትልቅ ለውጥ እንደተመዘገበበት ገልፀው፣ መንግስት ትልቅ በጀት መድቦ ለትግበራው እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የግል ዘርፉ፣ የሲቪል ማህበራትና የመንግሥታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ አጋር አካላት ድጋፍና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።
በሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ምዕራፍ ፍኖተ ካርታ ላይ የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን ለመተግበር 146 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ነዋይ ይጠይቃልም ነው ያሉት።
በዚህም የክልሎችን መዋጮ ጨምሮ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ መንግስት 6 ቢሊዮን ብር፤ በተመሳሳይ ከለጋሽ እና አጋር አካላት 6 ቢሊዮን ብር፤ በድምሩ 12 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።