በሚቀጥሉት አስር ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የተሻለ የደመና ሽፋንና የዝናብ ስርጭት ይኖራል-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የተሻለ የደመና ሽፋንና የዝናብ ስርጭት ይኖራል-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2016(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የተሻለ የደመና ሽፋንና የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በመደበኛ ሁኔታ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀስ በቀስ እየተጠናከሩ ይሄዳሉ፡፡
በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የተሻለ የደመና ሽፋን የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ጠቁሟል፡፡
በተለይ በደቡብ ምስራቅ፣ ሰሜን ምስራቅ እና መካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አመላክቷል፡፡
ይህም የአፈር ውስጥ እርጥበትን በማሻሻል ለበልግ ማሳ ዝግጅት የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጥርም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት እንዲሁም ለግጦሽ ሳርና መጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
ይህንን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልም የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ኢንስቲትዩቱ መልዕክት አስተላልፏል፡፡