የደብረ ብርሃን - አንኮበር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ብርሃን - አንኮበር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2016(ኢዜአ)፦ የደብረ ብርሃን - አንኮበር 42 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ዋና ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
አሁን ላይ ከግንባታው አጠቃላይ ሥራ 98 በመቶው ተጠናቋል ያለው አስተዳደሩ ቀሪ ውስን ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ ነው ብሏል፡፡
ከግንባታ ሥራዎች መካከል የ39 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦ፣ ሰብቤዝ ፣ የመንገድ ዳር የአደጋ መከላከያ አጥር እንዲሁም የትራፊክ ጠቋሚ ምልክቶች የማቅለም ሥራዎች መከናወናቸውን አመላክቷል፡፡
ግንባታው በሀገር በቀሉ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን እየተከናወነ መሆኑን ጠቁሞ የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
የፕሮጀክቱ በጀት በፌዴራል መንግስት የሚሸፈን መሆኑንም አስተዳደሩ ገልጿል።
መንገዱ በጠጠር ደረጃ ተገንብቶ ላለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ያስታወሰው አስተዳደሩ ከአገልግሎት ብዛት አኳያ መጎዳቱን ጠቁሟል።
በተጨማሪም የቦታው አስቸጋሪ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ በጠጠር ደረጃ ለነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አመቺ አለመሆኑ እንዲሁም ያለው በርካታ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ ገብቶ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል ብሏል፡፡
ከዚሁ የደብረ ብርሃን-አንኮበር የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተጨማሪ የአንኮበር-ዱለቻ እና የዱለቻ-አዋሽ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡
ሶስቱም ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ከዚህ ቀደም ወደ አፋር ለመሄድ ይወስድ የነበረውን ረጅም ርቀት እና ጊዜ ለማሳጠር እንደ አማራጭ እንደሚያገለግሉም ተመላክቷል፡፡
አካባቢው የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶችን በውስጡ የያዘ በመሆኑ መንገዱን ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ በኩል ግንባር-ቀደም ሚና ይጫወታልም ነው ያለው አስተዳደሩ ባወጣው መረጃ፡፡
በተጨማሪም ምቹ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር በማስቻል የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያቃልል ከመሆኑም ባሻገር ምርት በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲደርስ በማስቻል የአርሶ-አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚጨምርም አመላክቷል፡፡