ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታ ስራን አጠናቆ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች ልየታ ስራን አጠናቆ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆንበትን ነጻ የስልክ ቁጥር እና ድረ ገጽም ይፋ አድርጓል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ሁሉንም አካል አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ህብረተሰቡ ጋር ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች የተሳታፊ መረጣና ልየታ ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የሚከናወኑ ቀጣይ ስራዎችን በሚመለከት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ እንዲሆኑ አምስት ስብሰባዎች መደረጋቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ አሁን ላይ የተሳታፊ ልየታ ስራን አጠናቆ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል።

በቀጣይ ምዕራፍ በፌዴራል፣ በክልሎች እና በውጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡ ጋር መረጃ ለመለዋወጥ የሚውሉ 8112 ነጻ የስልክ ጥሪ አገልግሎት እና አጭር የጽሁፍ መልእክት መቀበያ፣ የመረጃ ዴስክ እንዲሁም http://ethiondc.org.et/ ድረ ገጽን በይፋ አስጀምሯል።

የነፃ መስመሩን በመጠቀም የተለያዩ ሃሳቦችን ለኮሚሽኑ መስጠት እንደሚቻልም ነው በዚሁ ጊዜ የተገለጸው፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም