ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተደብቆ የቆየውን የጥቁር ህዝቦች የድል ታሪክ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው - አምባሳደር ጥሩነህ ዜና

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2016 (ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተደብቆ የቆየውን የጥቁር ህዝቦች አኩሪ የድል ታሪክ ለዓለም የሚያስተዋውቅ መሆኑን አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ተናገሩ።

የኢትዮጵያውያንን የድል ብስራትና የጥቁር ህዝቦችን የነጻነት ታሪክ የሚዘክረው የአድዋ ድል መታሰቢያ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቆ ተከፍቷል።

በምርቃት ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአድዋ ድል ኢትዮጵያን የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ያደረገና በልዩነት ስሟን ያስጠራ አኩሪ ታሪክ  ነው፡፡


 

አድዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ጥቁር አፍሪካውያንም የይቻላል መንፈስን በማጎናጸፍ መነቃቃትን መፍጠሩንም ነው ያስታወሱት፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ስም በአፍሪካ ሀገሮች ብቻ ሳይሆን እስከ ካሪቢያን ገኖ እንዲወጣ ማድረጉንም እንዲሁ፡፡

ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የሆነውን የዓድዋ ድል ተገቢውን ቦታ በመስጠት ከማስተዋወቅ አንጻር ውስንነቶች እንደነበሩም ተናግረዋል።

በመሆኑም የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተደብቆ የቆየውን ታሪክ የበለጠ ለዓለም በማስተዋወቅ ለኢትዮጵያውያንና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሚሆን ነው ብለዋል።


 

"ዓድዋ የኛ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች ኩራት ነው"  ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ በመታሰቢያ ስፍራው የፓን አፍሪካን ሃውልት መቆሙ አድዋ ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትስስር ለማሳየት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት ባልተስፋፋበት በአንድነትና በህብረት ሀገራቸውን ከወራሪ ኃይል ነጻ ያወጡበትን ታሪክ በማስቀጠል የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ድህነትን ለመዋጋት በጋራ መቆም አለበት ብለዋል።

ቀደምት አባቶች ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚሆን ታሪክ ሰርተው ማለፋቸውን በማስታወስ፤ የአሁኑ ትውልድ በምጣኔ ሃብትና ዲፕሎማሲ ለአፍሪካ የሚተርፍ ታሪክ መስራት እንዳለበትም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ በ5 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባና አምስት ወለል ያለው ሲሆን፤ በዋናው መግቢያ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ የነጻነት ድል መገለጫ የሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሃውልት እንዲሁም የሁሉም ከተሞች ርቀት ልኬት መነሻ 0-0 ኪሎ ሜትር ይገኛል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተባብረው አፍሪካ በራሷ አቅም መልማት እንደምትችል ያሳዩበት የህዳሴ ግድብ ተምሳሌታዊ ፏፏቴም በመታሰቢያው ውስጥ ይገኛል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም