ከዓድዋ ጀግኖች የነጻነትና ክብር እሴትን በመውረስ ዛሬም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ክብርና ብልጽግና በጋራ መቆም አለብን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2016 (ኢዜአ)፡-  ከዓድዋ ጀግኖች የነጻነትና ክብር እሴትን በመውረስ ዛሬም ለምግብ ሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ክብር በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአድዋ ድል መታሰቢያን መርቀው ከፍተዋል፡፡


 

በምረቃ መርሃ ግብሩም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር የሰው ልጅ የህይወት ጉዞ በእድልና ትግል የተሞላ ነው ብለዋል፡፡

እድልን ያለ ትግል መጠቀም እንችልም፤ ትግልም ያለ እድል ከንቱ ድካም ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያዊነት እድላችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአድዋ መታሰቢያ ደግሞ ታግለን ያሳካነው ድል ብለዋል፡፡

ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ የኢትዮጵያዊያን ፈተናዎች ምንጮች "ባዳ እና ባንዳዎች" ስለመሆናቸውም ተናግረዋል፡፡

ባዳና ባንዳዎች ዛሬም የብልጽግና ጉዟችን ፈተናዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ዓድዋ ጀግኖች ከምንም በላይ ሀገርን አስቀድመን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ክብር በጋራ መስራት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

የዓድዋ ጀግኖች መስዋእትነት የከፈሉት ለነጻነትና ክብር መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ የዓድዋ ጀግኖችን እሴት በመውረስ ለምግብ ሉዓላዊነት፣ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ክብር በጋራ መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ነጻነት ለመጠበቅ ደግሞ ሾተሉን ወደ አፎቱ መመለስ፤ ቁጣን ደግሞ ወደ ትዕግስት መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ጥንታዊያን አባቶቻችን ከነጻነት ባሻገር ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ጭምር ለማሳደግ ትልቅ ህልም ይዘው መስራታቸውን አስታውሰው፤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራችው "ፀሐይ" አውሮፕላንን ለአብነት አንስተዋል፡፡

"ፀሐይ" አውሮፕላን በዓድዋ መታሰቢያ በክብር መቀመጧንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ዛሬም ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ በዓለም ተወዳዳሪ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም