ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንቅስቃሴ ስኬታማነት ድርሻችንን እንወጣለን - የጅግጅጋ ከተማ የህብረተሰብ ተወካዮች

ጅግጅጋ ፤ የካቲት 3/2016(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንቅስቃሴ  ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ተወካዮች ገለጹ። 

ኮሚሽኑ ከፋፈን ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እና ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተወካዮችን ለማስመረጥ በጅግጅጋ ከተማ ያካሄደው መድረክ ተጠናቋል። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተወካዮች እንዳሉት ኮሚሽኑ የጀመረውን ሥራ ስኬታማ ለማድረግ የድርሻቸውን ይወጣሉ። 

ከተወካዮች መካከል ወይዘሮ ሀያት አብዲራህማን እንዳሉት ኢትዮጵያን አሁን ካሉባት ችግሮች አውጥቶ በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር የውስጥ ችግሮችን ተነጋግሮ በዘላቂነት ለመፍታት የኮሚሽኑ መቋቋም ወሳኝ ነው። 

ኢትዮጵያ የብዙ እምነቶች እና የብዘሃ ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ መሆኗን አስታውሰው፣ ይህን ጠብቆ በማቆየት የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። 

የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይ ሴቶችን በማንቃትና ግንዛቤ በማፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጾ እንደሚያደርጉ ወይዘሮ ሀያት ገልጸዋል። 


 

ኮሚሽኑ ለግጭትና ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ከታች ጀምሮ ለይቶ በምክክር እንዲፈቱ ያደርጋል ያለው ደግሞ ወጣት አብዲናስር ኑር ነው። 

"የምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን እኔም የበኩሌን እወጣለሁ'' ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች። 

በጅግጅጋ ከተማ የተዘጋጀው የህብረተሰብ ተወካዮች ምርጫ አስተባባሪ አቶ አሰድ ሼኽ አብዲራህማን አሊ እንዳሉት፣ በከተማው ከሚገኙ አራት ክፍለ ከተሞች 80 የህብረተሰብ ተወካዮች ተመርጠዋል። 


 

ተወካዮቹ ከሴቶች፣ ከእድር ማህበራት፣ ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከመምህራን፣ ከመንግስት ሠራተኞች፣ ከአካል ጉዳተኞችና በተለያየ ምክንያት ከተገፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በምርጫው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት የሂደቱን አካታችነትና አሳታፊነት ከማረጋገጥ ባለፈ ሁሉም አገራዊ ስሜት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ብለዋል። 

"እንደ አገር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መነጋገርና ችግሮችን በተረጋጋ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል" ያሉት አስተባባሪው፣ ለዚህ ደግሞ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይ በቀጣይ ለሚካሄደው ምክክር ስኬታማነት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ ተብሎ በተሳታፊዎች የታመነባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመድረኩ መመረጣቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሶማሌ ክልል አስተባባሪ አቶ አወሉ ሁሴን በበኩላቸው ኮሚሽኑ በፋፈን ዞን ወረዳዎችና በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባማከለ መልኩ ስኬታማ ምርጫ ማከናወኑን ገልጸዋል።

በእያንዳንዱ አደረጃጀት ሁለት ሁለት ተወካዮች መመረጣቸውን ገልጸው በቀጣይም የቶግውጫሌ ከተማ ተወካዮች ምርጫ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም