ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ምርቶቻችንን ከማስተዋወቅ ባሻገር ለገበያ ትስስር ምቹ እድል ፈጥሮልናል-ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2016(ኢዜአ)፡-  አገር አቀፍ የህብረት ስራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር ለገበያ ትስስር ምቹ እድል እንደፈጠረላቸው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

10ኛው አገር ዓቀፍ የህብረት ስራ ኤግዚቢሽንና ባዛር “የህብረት ስራ ማኅበራት ከገበያም በላይ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡ 

በኤግዚቢሽንና ባዛሩም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የህብረት ስራ ማህበራት ተሳትፈዋል፡፡


 

በሲዳማ ክልል የጋምቤላ ኃላፊነቱ የተወሰነ የአናናስ አምራችና ግብይት መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር ሊቀመበር አቶ  አላዛር ፈጌ ፤ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ጥራቱን የጠበቀ አናናስ ለገበያ ማቅረባቸውን  ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የገበያ ትስስርና መደረሻ በመፍጠርም በቀጣይ በቋሚነት የአናናስ መርት ለማቅርብ መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡


 

የኢትዮ ኢንጂነሪግ ጉርፕ ተዋካይ አቶ ፍቃዱ ዱቤ በበኩላቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አምራቾችና ሸማቾችን ለማገናኘትና በተመሳሳይ ዘርፍ ከሚሳተፉ ድርጅቶች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዳገዛቸው ጠቁመዋል፡፡

በአፋር ክልል የጋሊኮማ ኅብረት ሥራ ዩኒዬን ሊቀመንበር መሐመድ ኑር እና የዳንካሌ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒዬን ሊቀመንበር አህመድ አደም እንደገለጹት፤ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡


 

በተለይም በክልል የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረጉን አውስተዋል፡፡

ህብረት ስራ ማህበራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ግንኙነትን ከማጠናከር በላይ የፋይናስ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ ናቸው፡


 

ከዚህ አኳያ ኢግዚቢሽንና ባዛሩ ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር  ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 219 ሸማችና አምራች ህብረት ስራ ማህበራት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው በዚህም 30 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርት ለግብይት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

አገር አቀፍ የህብረት ስራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን፤ እስከ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም