የአልትራሳንውንድ ህክምና መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአልትራሳንውንድ ህክምና መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2016(ኢዜአ)፡- የአልትራሳንውንድ ህክምና መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ።
ፋብሪካው በአዲስ አበባ ጋርመንት በሚገኘው ሁዋጂያን ኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ ተመርቆ በዛሬው እለት ስራ ጀምሯል።
በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ፣ የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጀርመንና የእስራኤል አምባሳደሮችን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የአልትራሳውንድ መገጣጠሚያ ፋብሪካው የተለያዩ ዓይነት ህመሞችን መመርመር የሚያስችል መሳሪያዎች የሚገጣጠሙበት ሲሆን ኤልስሜድ ሶሊሽንስና ሲመንስ የተሰኙ ኩባንያዎች በጋራ ኢንቨስት አድርገዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ፤ የፋብሪካው ወደ ሥራ መግባት ከኢትዮጵያም ባለፈ በአፍሪካ በላቀ ቴክኖሎጂ ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ፋብሪካው በተለይም በህክምና ዘርፍ ለተሰማሩ ቴክኒሻኖች፣ መሃንዲሶችና ደጋፊ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ወሳኝ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
የኤልስሜድ ሶሉሽን ኩባንያ ፕሬዝዳንት ሮኔን ባሁር በበኩላቸው ከረጅም ዓመታት ዝግጅት በኋላ የፋብሪካው እውን መሆን አስደስቶናል ብለዋል።
ለፋብሪካው እውን መሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቁን ድርሻ የሚወስድ መሆኑን ጠቅሰው አድናቆታቸውንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ያደረግነው ኢንቨስትመንት ሌሎች ኩባንያዎችን ኢትዮጵያን ተመራጭ መዳረሻ እንዲያደርጉ በር እንደሚከፍት ተናግረዋል።
የኤልስሜድ የኢትዮጵያ ተወካይ የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው በፋብሪካው የሚመረቱ ማሳሪያዎች በኢትዮጵያ የተሰራ /ሜድ ኢን ኢትዮጵያ/ መለያ ብራንድ የሚጻፍባቸው በመሆኑ ለኢትዮጵያ ኩራት ነው ብለዋል።