የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በስድስት ወራት 27 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በስድስት ወራት 27 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 27 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የስራ ከንውንና ቀጣይ እቅዶቹን በማስመልከት ኢዜአ ከተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር ) ጋር ቆይታ አድርጓል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ተቋሙ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው በለውጡ ሂደት በተከናወነው የተቋም ግንባታ ስራ ወደ ውጤታማነት መሸጋገሩን ገልጸዋል።
የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በገቢም ይሁን በትርፋማነት በስኬታማነት ቀጥሏል ብለዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከእቅዱ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ 27 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
ለተገኘው ውጤትም በመንግስት አቅጣጫ የተቋም ግንባታ በመከናወኑና ቀልጣናፋ ዘመናዊ አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የስምሪትና ቁጥጥር ስራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸው፤ አገር አቋራጭ የመርከብ ንግድ ስራዎች መስፋታቸውና ወጪን የቀነሰ አሰራርን መከተሉ ለውጤት አብቅቶታል ብለዋል።
በቀጣይም የገቢና ወጪ አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ የማድረግ ስራ እና የመርከብ መዳረሻዎችን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዶክተር በሪሶ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አሁን ላይ በ345 የወደብ መዳረሻዎች የወጪ እና ገቢ ንግዱን በማሳለጥ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።