የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ሥምምነት ቀጣናዊ ልማትና ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ሥምምነት ቀጣናዊ ልማትና ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ ፤ የካቲት 2/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ሥምምነት ለቀጣናው ልማትና ትብብር መጠናከር ወሳኝ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ ዋነኛ ፍላጎት ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ መልማት ነው ብለዋል።
የቀጣናው አገራት በብዙ መንገድ የተሳሰሩ መሆናቸውን በማንሳት ይህንን ትስስር በጋራ ልማት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ፤ የቀጣናው አገራት ሕዝቦች በባህል፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች የተቆራኙ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነትና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ቀጣናው የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል በመሆኑ ሥምምነቱ ለኢትዮጵያና ለሶማሊላንድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባለፈ ዓለም አቀፍ ጠቃሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማትና ለመበልጸግ ጽኑ መሻት ያላት መሆኑን መረዳትና መደገፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የሶማሊያ መንግሥትም ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ ግንኙነትን አጥብቃ የምትፈልግ መሆኑን በመገንዘብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ ጉዳይ አንድ አይነት አቋም በመያዝ ለምጣኔ ኃብት እድገትና ጠንካራ አገር ለመገንባት በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።