የባህርዳር ከተማን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የፀጥታ አካላት በትጋት ሊሰሩ ይገባል- ኮማንድ ፖስቱ - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ከተማን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የፀጥታ አካላት በትጋት ሊሰሩ ይገባል- ኮማንድ ፖስቱ

ባህርዳር፤ የካቲት 2 / 2016 (ኢዜአ)፡- ባህርዳር ከተማ ሰላሟን አስጠብቃ ልማቷ ላይ እንድታተኩር የጸጥታ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የባህርዳር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ አሳሰቡ።
"ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ለፀጥታ አካላት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ የስልጠና መርሃ ግብር ተጠናቋል።
ስልጠናው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አመራርና አባላት እንዲሁም ለዘርፉ ባለሙያዎች የተዘጋጀ መሆኑ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በስልጠናው ማጠናቀቂያ የተገኙት የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የባህር ዳር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሜጄር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለ10 ቀናት የተሰጠው ስልጠና የፀጥታ ኃይሉን ወታደራዊ አቅምና ብቃት ያጠናከረ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ የራሱን ሰላም በራሱ የፀጥታ ኃይል ለመሸፈን የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህ ኃይል ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የኮማንድ ፖስቱ አባል አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው፤ በከተማዋ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ይህ ኃይል የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ባህርዳር ከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ ብትሆንም ተፈጥሮ በነበረው ችግር እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ እንደቆየ ጠቅሰዋል።
የፀጥታ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ባደረገው ጥረት "የተገኘውን ሰላም ለማስከበርና ልማቱ እንዲፋጠን ሁላችንም የድርሻችን ልንወጣ ይገባናል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ሃምሳ አለቃ ግርማ ጌታሁን በሰጡት አስተያየት፤ በ10 ቀናት የስልጠና ቆይታቸው አቅማቸውን በበቂ ሁኔታ የገነባ ትምህርት እንዳገኙ ተናግረዋል።
በዚህም "የከተማዋን፣ የክልሉንና የኢትዮጵያን ሰላም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
በቆይታቸው በቂ ስልጠና እንዳገኙ የገለፁት ደግሞ የሰላም አስከባሪ ሚሊሽያ አባል አማረ ታደሰ ናቸው።
ከዚህ በኋላ የከተማዋን ብሎም የክልሉ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን "ከትግል ጓዶቼ ጋር ሌት ተቀን ያለመሰልቸት ህዝቤን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ" ሲሉ ገልጸዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ከፍተኛ መኮንኖችና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አባላት ተገኝተዋል።