ቀጥታ፡

ከተሞች  የመሬት መረጃዎችን ማዘመንና አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባቸዋል 

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 2/2016 (ኢዜአ)፦ ከተሞች የመሬት መረጃዎችን ማዘመንና አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር አሳሰበ።  

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በካዳስተር ሥራዎችና መልካም ተሞክሮዎች ዙሪያ የከተሞችና የክልሎች የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዳማ ተካሂዷል። 

የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ደጀን በዚሁ ጊዜ በከተሞች መሬትን የመመዝገብ፣ የማልማትና የማስተዳደር ሥራዎች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል። 

መሬትን በካዳስተር ሥርዓት መመዝገብ ለከተሞች ዕድገትና ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ከተሞች ዘመናዊ ሆነው እንዲያድጉና እንዲለሙም ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ያም ብቻ ሳይሆን የዜጎች የይዞታ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም ጠቁመው አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳም ገልጸዋል።  

የመሬት መረጃዎችን ማዘመንና አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው  ከተሞች ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ለከተሞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።  


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር አህመዲን መሃመድ በበኩላቸው በክልሉ የካዳስተር ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ካዳስትርን ወደ ሥራ ለማስገባት ከከተሞች ጋር የመነጋገር ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸው እንደ ደብረብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደርና ባህርዳር ያሉ ከተሞች ላይ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ጠቁመዋል። 


 

የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍቃዱ ሽፈራው በበኩላቸው በክልሉ 42 ከተሞች የካዳስተር ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

ከዚህ ውስጥም በ37 ከተሞች ላይ መሬትን የመመዝገብና በካዳስተር ሥርዓት የማስተዳደር ሥራ   መጀመሩን ጠቁመዋል። 


 

የሀረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አሚና አብዱልከሪም፣ በክልሉ ለካዳስተር ሥርዓት ትግበራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መሟላታቸውን ተናግረዋል። 

ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉ ብቁ የሆኑ የሰው ኃይል መዘጋጀታቸውንም ጠቁመው ለሕዝቡም ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።  

መሬትን በካዳስተር ሥርዓት መመዝገብ የከተማ ገቢን ከማሳደግ በተጨማሪ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከልም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በመድረኩ ተጠቁሟል።  

በመድረኩ የክልል መሬት ቢሮ ኃላፊዎችና ምክትል ቢሮ ሃላፊዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም