አድዋ በፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
አድዋ በፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንደበት

(በአየለ ያረጋል)
ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የስበት ማዕከል ናት። የቀደምት ዘሮቻቸው እትብት መሰረት፣ የትናንት ስልጣኔያቸው ምሳሌ፣ የነገ ተስፋቸው ፋና አድርገው ይወስዷታል። ከአፍሪካ እስከ ካረቢያን ሀገራት ጥቁር ልሂቃን ኢትዮጵያ ቀደምት እናታችን ሲሉ ይደመጣሉ። አፍሪካዊያን ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ በወሰደው የነጻነት ተጋድሏቸው ወቅት 'ስሟን' ተውሰዋል። የሰንደቋን ቀለማት የድሕረ ነጻነት ዓርማቸው አድርገው ወርሰዋል። በኋላም የመላው አፍሪካዊያን የጋራ ተቋም በአዲስ አበባ መስርተዋል። በተለይም የፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ መሪዎች ለኢትዮጵያ ልዩ ስሜት፣ ክብርና ምኞት አላቸው።
የአፍቅሮተ-ኢትዮጵያ አንዱ እና ቁልፉ አመክንዮያቸው ደግሞ የአድዋ ድል ነው። የፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ ፋና ወጊዎቹ አድዋ የአፍሪካዊያን ትንሳኤ ብሎም ለሰው ልጅ መንፈስ ጥንካሬ ምስክር እና ወደር የለሽ ድል መሆኑን አውስተዋል። ከዕውቅ ፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ምሁራን እና ፖለቲከኞች መካከል ስለአድዋ ያሉትን እናውሳ!!
የዘር ግንዱ ከአፍሪካ የሚመዘዘው ትውልደ አሜሪካዊ ታላቁ የታሪክ ምሁርና የሐርቫርድ ምሩቅ ዶክተር ዊልያም ኤድዋርድ ዲዩቦይስ ከፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ ፋና ወጊዎች አንዱ ናቸው። ምሁሩ "የኢትዮጵያ ኮኮብ"(ስታር ኦቭ ኢትዮጵያ) በሚል ሺዎች በተሰበሰቡባቸው አደባባዮች አትዮጵያን ጨምሮ ስለጥቁር ህዝብ ታሪክ፣ ተስፋና ስልጣኔ የሰብኩ ናቸው። በአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 1900 በለንደን በነበረው የመጀመሪያው የፓን አፍሪካ ጉባዔም የኢትዮጵያን ስም በጉልህ አንስተዋል። ይህም ከአድዋ ድል ማግስት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወቅት ነበር። ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ማግስት በአውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር ነሐሴ ወር 1963 በጋና-አክራ ከተማ ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈው ዶክተር ዊልያም አድዋን እንዲህ ይገልጹታል።
"አድዋ በቅኝ ግዛት ትግል አይበገሬ መንፈስ ላላቸው እንዲሁም ለነጻነታቸው ፋና ወጊ ለሆኑ አፍሪካዊያን ህዝቦች ምስክርነት የቆመ ድል ነው"
ሌላው ስመ ጥር የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኙ ትውልደ ጀማይካዊው ማርከስ ጋርቬይ ነው። ዕውቁ 'የምልሰተ-አፍሪካ' ሀሳብ ወጣኝ፣ የጥቁሮች መብት ታጋይ እና የዓለም አቀፍ ጥቁሮች ሕብረት እና የአፍሪካ ማህበረሰብ ሊግ መስራችና ቀዳሚው ፕሬዝዳንት ነው። ጋርቬይ ስለአፍሪካ እና ስለአፍሪካ ዳያስፖራ ትስስር በአያሌው የሞገተ፣ በአሜሪካ እና አውሮፓ ፓን አፍሪካዊያን በማሰባሰብ ትለቅ ንቅናቄ የፈጠረ፣ በሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ወቅት ስለኢትዮጵያ ነጻነት የታገለ ፓን አፍሪካዊ ፖለቲከኛ ነው። ይህ ስመ ጥር ፖለቲከኛ አድዋን እነዲህ ይገልጸዋል።
"የአድዋ ድል ማለት ጥቁሮች ትልቅ ስኬት ለማስመዝገብ ብቁ እንደሆኑ ብሎም ዝቅ ተደርገው መቆጠር እንደሌለባቸው ለዓለም ያረጋገጠ ድል ነው"
የዓለማችን ብርቱው ሰው፣ የሕግ ምሁር፣ የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪ፣ የነፃይቱ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ፣ የዓለም የሠላም ሎሬት ኔልሰን ማንዴላ መቼስ ለኢትዮጵያ የተለዬ ፍቅር፣ ክብርና ስፍራ ካላቸው ታላላቅ አፍሪካዊ ግለሰቦች አንዱ ናቸው። 'ረጅሙ የነጻነት ትግል ጉዞ' በተሰኘው ግለ ታሪካቸውም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ከበሬታ በጉልህ አንጸባርቀዋል። ታላቁ የአድዋ ድል በማንዴላ አንደበት እንዲህ ይገለጻል።
"በአድዋ ላይ የተገኘው ድል ወታደራዊ ድል ብቻ አይደለም። ይልቁኑም መንፈሳዊ ድል ጭምር እንጂ"
ሌላው የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ ስለአድዋ ታሪካዊ ድል በስፋት ሲያወሱ ይታወቃሉ። በአንድ ወቅትም በአድዋ ድል ክብረ በዓል ዕለት በአድዋ ከተማ ታሪካዊ ስፍራ በአካል ተገኝትው ስለአድዋ ታላቅነት ተናግረዋል። የአድዋ ድል በምቤኪ አንደበት እንዲህ ይገለጻል።
"ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ላይ ያገኙት ድል አፍሪካ በቀጥታ ቅኝ ግዛት ቀንበር መንበርከክ አለባት የሚለውን የበርሊን ውሳኔን በቀጥታ ያከሸፈ ድል ነው። ኢትዮጵያዊያን አፍሪካ በቅኝሽ ግዛት አትንበረከክም ብለው ተነሱ፤ ድልም ነሱ"
በተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ብሎም የሀገሪቷ የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ መሪው፣ የሕብረተሰባዊት ኮንጎ አብዮተኛው እና ዕውቁ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ፓትሪስ ሉሙምባ አደዋን በከፍታ ይጠቅሱታል።
"አድዋ አፍሪካ ለአፍሪካዊያን ብቻ የተገባች እንደሆነች እንዲሁም እኛ አፍሪካዊያን መዳረሻ ግባችንን ራሳችን መወሰን የምንችልበት አቅም እንዳለን ያስታወሰን ድል ነው"
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልና የድሕረ ነፃነት የጋና የመጀመሪያው መሪ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቁልፍ ተዋናይ የሆኑት ዕውቁ ፖለቲከኛ ዶክተር ክዋሜ ንኩርማም አድዋን በቅጡ ገልጸውታል።
"የአድዋ ድል በአፍሪካ ታሪክ አዲስ ማስፈንጠሪያ ክስተት ነው። አፍሪካዊያን ወደ አንድነት በመሰባሰብ ቅኝ ገዥዎችን ድል ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ደል ነው"
በነገራችን ላይ ታላቁ የነፃነት ታጋይ፣ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ እና የቀድሞ የጋና ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩዋሚ ንኩርማ በሚያዝያ 1963 በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት) ምስረታ ወቅት ያደረጉትን ንግግር ከጨረሱ በኋላ መሰናበቻቸው ኢትዮጵያን የሚያወድስ እና የሚዘከር "Ethiopia shall rise-ኢትዮጵያ ትነሻለሽ" በሚል ርዕስ ግጥም በመቀኘት ነበር።
Ethiopia, Africa’s bright gem
Set high among the verdant hills
That gave birth to the unfailing
Waters of the Nile
Ethiopia shall rise
Ethiopia, land of the wise;
Ethiopia, bold cradle of Africa’s ancient rule
And fertile school
Of our African culture;
Ethiopia, the wise
Shall rise
And remould with us the full figure
Of Africa’s hopes
And destiny.
ይህን ታሪከዊ ግጥም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ትምህርት እና የስነ ማስተማር ተመራማሪና መምህር ዶክተር ውቤ ካሳዬ በ2002 ዓ.ም "ኢትዮጵያ ታብባለች" በሚል ርዕስ እንዲህ ተርጉመውታል። (ከዚህ ፅሁፍ ፀሐፊው ጥቂት የቃላት ለውጥ ጋር እነሆ)።
ኢትዮጵያ ታብቢያለሽ!
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ፈርጥና ጌጥ
በውብ ተራሮችሽ፣ ወንዞች፣ ሜዳዎችሽ
እንዲሁም ለምለም ጨዋ እምብርትሽ
ተንቆጥቁጠሽ አምረሽ፣ ትታያለሽ ደምቀሽ፣
ከፍ ብለሽ አብበሽ።
በዓባይ ታላቅ ወንዝሽ ጉልበት የዘመናት ቅርስሽ
ለዝንተ-ዓለም ለሚፈሰው፣ ምድረ ግብፅና ኑቢያን በሚያጠግበው
ትነሻለች ታብቢያለሽ።
የአፍሪካ ጥንተ ስልጣኔ መገኛ፣ ምድረ-ጠቢባን ኢትዮጵያ፣
የአፍሪካችን ባህል ምኩራብ፣ የጥበብ ማዕድ ባለቤት የአንድነት አምሳያ፣
ጥበብ በጥበብ ደርበሽ ደራርበሽ፣ ትነሻለች ታብቢያለሽ።
በአዲስ መንፈስ ከነ ምሉዕነትሽ ትነሻለሽ፣
የአፍሪካን ግብ ሰንቀሽ፣ የአፍሪካን ተስፋ ይዘሽ።