የአድዋ ድል መታሰቢያ የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ነው - አባት አርበኞች - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል መታሰቢያ የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ነው - አባት አርበኞች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክ ሰሪዎችን ያከበረና ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ትልቅ ሥራ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አባት አርበኞች ገለጹ።
ታሪኩን በሚመጥን መልኩ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታው ተጠናቋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን፣ የአድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ፣ የአንድነት ማዕከል፣ የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ እንዲሁም የጀግኖችን ጉዞ የሚያሳዩ ድንቅ የታሪክ አሻራዎችን በውስጡ ይዟል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ መሆኑን ነው መታሰቢያውን የተመለከቱ አባት አርበኞች የገለጹት።
አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ እንዳሉት፤ ለአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት ለሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ ታሪክ የሰሩትን በማክበር ትውልዱ በቀጣይ ሌላ አገርን የሚጠቅም ታሪክ እንዲሰራ የሚያግዝ ነው።
የአድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ በተለይም ለወጣቱ ትልቅ ቅርስና የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ወጣቱ የልማት አርበኛ በመሆን ሳይሰለች አገሩን ማገልገልና የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ማስጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
አባት አርበኛ ሃምሳ አለቃ ዲባባ ጫላ በበኩላቸው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሁሉንም ታሪኮች አሟልቶ የያዘና ትውልዱ የሚማርበት ትልቅ ሥራ መሆኑን አመልክተዋል።
አድዋ የደም ዋጋ የተከፈለበትና የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት እንዲሁም የድል ምልክት ነው ያሉት አባት አርበኛው መታሰቢያው የተሰራውን የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ የሚያቆይ ነው ብለዋል።
አባት አርበኞቹ ወጣቱ ትውልድ የአድዋ ድል መታሰቢያን በአግባቡ በመጠበቅ ለትውልድ ማሻገር እንዳለበት አሳስበዋል።