በመሰረተ ልማት ስርቆት ሳቢያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ባጠረ ጊዜ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በመሰረተ ልማት ስርቆት ሳቢያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ባጠረ ጊዜ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል
ጂንካ ፤ የካቲት 2/2016(ኢዜአ)፦ በመሰረተ ልማት ላይ በደረሰ ስርቆት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ባጠረ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ሳውላ ሜላ ቀበሌ አካባቢ በሚገኝ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ምክንያት በአምስት ዞኖች የኃይል አቅርቦቱ ተቋርጧል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ አሪ ዞን፣ ባስኬቶ ዞን ሙሉ በሙሉ እና ጋሞ ዞን በከፊል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ የተቋረጠባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በስርቆቱ ምክንያት አደጋ የደረሰባቸውን መስመሮች ለመጠገን አገልግሎቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኃይል የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ባጠረ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ጥገናው ተከናውኖ ወደ አገልግሎት እስኪመለስ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅም ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
አቶ ሞገስ አክለውም ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ በፀጥታ ሀይሉ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችም ለህግ እንዲቀርቡ የአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ የፀጥታ ኃይሉ ርብርብ እንዲያደርጉም አመላክትዋል።