በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2016(ኢዜአ)፦ በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን በድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ፡፡
በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ከደቡብ አፍሪካ ጋር አካሂዶ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት አጠናቋል።
በዚህም ብሔራዊ ቡድኑ 3 ለ 0 በሆነ የድምር ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
ሉሲዎቹ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን 3 ለ 0 ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን፤ በቀጣይ የሦስተኛ ዙር ጨዋታውን ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርግ ይሆናል።
ስምንተኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በካሪቢያኗ አገር ዶሚኒካን ሪፐብሊክ አዘጋጅነት እ.አ.አ ከጥቅምት 16 እስከ ሕዳር 3 2024 ይካሄዳል።
በዓለም ዋንጫው አዘጋጇን ዶሚኒካን ሪፐብሊክ ጨምሮ 16 አገራት የሚሳተፉ ሲሆን በውድድሩ ለመካፈል በስድስት አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች የማጣሪያ ጨዋታዎች በማድረግ ላይ ናቸው።
በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) በዓለም ዋንጫው ሶስት አገራትን የማሳተፍ ኮታ በተሳጣት አፍሪካም የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ይገኛል።
የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ በአራት የጥሎ ማለፍ ዙር እንደሚካሄድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።