ቀጥታ፡

ፍርድ ቤቶች ለሕዝቡ የሚሰጡት አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በሰው ኃይልና በመሰረተ ልማት እራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይኖርባቸዋል-አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2016 (ኢዜአ)፡- ፍርድ ቤቶች ለሕዝቡ የሚሰጡት አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በሰው ኃይል፣ ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂና በምቹ መሰረተ ልማት እራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ተክለ ኃይማኖት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለመገንባት ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ የሕንጻ ግንባታውን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።


 

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ፍርድ ቤቶች ለሕዝቡ የሚሰጡት አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ በሰው ኃይል ጊዜውን በዋጀ ቴክኖሎጂና በምቹ መሰረተ ልማት እራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ አንጻር በዛሬውም ዕለት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ለኅብረተሰቡ ምቹና ቀልጣፋ የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው የገለጹት።

ለፍርድ ቤቶች ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ብቻ የሕዝብን የፍትህ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ የሚመልስ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባኤው የፍርድ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች እራሳቸውን በክህሎትና በእውቀት ማጎልበት አለባቸው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በሥነ-ምግባር የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው በአገሪቱ ለዜጎች የፍትህ ተደራሽነትን ለማስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ የመሰረተ ልማት መሟላት አይተኬ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻን መገንባት በዘርፉ ላይ ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።


 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ በበኩላቸው የዋና መሥሪያ ቤቱ መገንባት ሁሉም ምድብ ችሎቶች አንድ አካባቢ ላይ በመሆን የዳኝነት አገልግሎትን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ የሕግ ጉዳዮችን የሚቀርቡ መሆኑን አስታውሰው በሚቀርቡ ጉዳዮች ልክ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ምላሽ እንዲያገኙ በር ይከፍታል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም