ቀጥታ፡

ጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ከ97 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

ሀዋሳ ፤ የካቲት 2/ 2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ከ97 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል።

ኮሚሽኑ የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸሙን በሀዋሳ ከተማ እየገመገመ ነው።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ተልእኮውን ለመወጣት እያከናወነ ባለው ተግባር ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም ከ97 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ገቢው ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከሱር ታክስ፣ ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች የተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ከወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው እቃዎች መያዙንም አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር ደበሌ በግምገማው የተገኙ ውጤቶችንና ጉድለቶችን በመለየት ኮሚሽኑን ለተሻለ ውጤት የሚያበቁ ስራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በስራ ሂደት እያጋጠመ ያለውን ተግዳሮት በተገቢው በመገምገም፣ ውጤቱን በመመዘን ተቋሙን ወደ ተሻለ እድገት ለማሻገር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።


 

የኮሚሽኑ የስትራቴጂክ ፕላንና ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብዲሳ ዱፌራ የኮሚሽኑን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሥራ አስኪያጆች፣ ምክትል ሥራ አስኪያጆችና ሌሉች የሥራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኮሚሽኑ የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም