ቀጥታ፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት  እስከ ምሽት 1 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ ፤የካቲት 01/2016 (ኢዜአ)፡- የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተጨማሪ  የስራ ሰዓት ማሻሻያ አደረገ።

በሰዓት ማሻሻያ ይፋ ማድርጊያ መርሐ ግብር ላይ፣ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሚድ ኪኒሶ፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ፣ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር ጀነራል ዳመና ዳሮታና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በአይነትና በመጠን እየጨመረ ለመጣው የተገልጋዮች ፍላጎት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የስራ ሰዓት ማሻሻያ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን የጊዜ ቀጠሮን እንደሚያሳጥርና የስራ ጫናን እንደሚቀንስ ተጠቁሟል።


 

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሚድ ኪኒሶ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በአዲሱ የስራ ሰዓት ማሻሻያ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ መደበኛ አገልግሎት ጧት 2 ሰዓት ይጀመራል።

በምሳ ስዓት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከሰዓት ደግሞ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቅዳሜ ግማሽ ቀን ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ወደ ሙሉ ቀን መሻሻሉን አስታውቀዋል።

አገልግሎቱ በ15 ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቶች በቴክኖሎጂና በሌሎችም የአስራር ስርዓቶች በቀን በአማካይ ከ6 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን እንደሚያስተናግድ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም